fbpx

በመድኃኒት ችርቻሮ ላይ ያንዣበበው ተግዳሮት

የማይጠበቁ፣ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡና በጆሮ ለመስማት የሚሰቀጥጡ እኩይ ተግባራት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ሲፈጸሙ መመልከት የዕለት ተዕለት ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ እርግጥ ነው በማህበራዊ ጉዳይ ብዙ ተብሏል፡፡ ቤት ለማሳመር ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ጀሶ በእንጀራ መልክ እንድንመገብ ያደረጉ ስግብግብ ነጋዴዎች በህዝብ ላይ ግፍ ሠርተዋል፡፡ በፎርጅድ በተገኘ የትምህርት ማስረጃ ገንዘብ ስላላቸው ብቻ በርካታ ሀብታሞች በግንባታው ዘርፍ በመግባት ጥራታቸውን ያልጠበቁ ግንባታዎችን በማከናወን ሀገራዊ ክስረት እያደረሱ ናቸው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ በከተማዋ በአንዳንድ የመድኃኒት መደብሮች የጤና ባለሙያ ያልሆኑ መድኃኒት ቸርቻሪዎች ከፋርማሲ (መድኃኒት) ትምህርት ጋር ሳይተዋወቁ እንደሚቸበችቡ ደርሼበታለሁ ሲል አመላክቷል፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ፤ በከተማዋ በርካታ የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች ማለትም መድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ያሉ ሲሆን፤ ያልተፈቀዱ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ህገወጥ መድኃኒቶችን ከመሸጥ ባሻገር ምንም ዓይነት የመድኃኒት (የፋርማሲ) እውቀት ሳይኖራቸው በየመደብሮች መድኃኒት የሚሸጡ ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡

መድኃኒት መሸጥ የህክምና ምክር አገልግሎት መስጠትን ይጠይቃል፡፡ ይህም የሚገኘው ከጤና ባለሙያዎች ብቻ ነው፡፡ መድኃኒት ማንኛውም ሰው በሱቅ ላይ የሚሸጠው ሸቀጥ አይደለም ያሉት ወይዘሮ አለምፀሐይ፤ በከተማዋ እየታየ ያለው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ አንዳንድ መድኃኒት መደብሮች ባለሙያ ያልሆኑ ወጣት ሴቶችን በመቅጠር ወይም ሙያ የሌለውን ቤተሰብ በሻጭነት በመመደብ መድኃኒት እንዲሸጡ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው በማለት ይናገራሉ፡፡

ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች መድኃኒት ሲሸጡ ዶክተሮች ከሚጽፉት ማዘዣ በተቃራኒ የመድኃኒቶችን አጠቃቀም አዛብተው በመጻፍ በህይወት ላይ አደጋ ያስከትላሉ፡፡ በዚህ ተግባር ሲሳተፉ የተገኙ ሁለት የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው ሙሉ በሙሉ የተሰጣቸው የሥራ ፈቃድ ተሰርዞባቸዋል በማለት ወይዘሮ አለምፀሐይ አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ አለምፀሐይ ገለጻ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመድኃኒት ችርቻሮ ፈቃድ ወስደው እየሠሩ በሚገኙ 780 ተቋማት ላይ በተደረገው መደበኛ ቁጥጥርና ፍተሻ ህገወጥ መድኃኒት ማለትም ያልተመዘገቡ፣ ደረሰኝ የሌላቸውና የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸውን ይዘው የተገኙ 79 የጤና ተቋማትና መድኃኒት ቸርቻሪ መደብሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ እንዲሁም በ312 ተቋማት በተሠራ የኦዲት ምርመራ 32 ተቋማት ችግሮች በመገኘታቸው በአጥፊዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

በህጋዊ እርምጃዎቹ መድኃኒቶች እንዳይሸጡ ተለይተው እንዲቀመጡ የተደረገ ሲሆን፤ በአስተዳደራዊ እርምጃ አራት የመድኃኒት ሻጭ ድርጅቶች የሙያ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ተሰርዞባቸዋል፡፡

ወይዘሮ አለምፀሐይ «በከተማዋ ከሚገኙ የጤና ተቋማት 10 በመቶ የሚሆኑት ግብዓት በአግባቡ ከመጠቀም፣ በደረጃቸው አገልግሎት ከመስጠት፣ መድኃኒቶችን በአግባቡ ማስቀመጥና ቆሻሻን በአግባቡ መያዝና ማስወገድ ላይ ክፍተቶች አሉባቸው፡፡ እንዲሁም ህጋዊ ምንጫቸው የማይታወቅና በሀገር ውስጥ ያልተፈቀዱ መድኃኒቶችን የሚይዙ የመድኃኒት መደብሮችም ተለይተዋል» ብለዋል፡፡

የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሀገራዊ የጤና ተቋማት መመዘኛ (ስታንዳርድ) ወጥቶ ፈቃድ በደረጃ በመውሰድ እንዲሠሩ ለማድረግ በ2006 እና 2007 በጀት ዓመት በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን፤ በ2006 በጀት ዓመት በወጣው መመዘኛ መሰረት 122 የጤና ተቋማት በቀይ ምልክት ደረጃ ነበሩ፡፡ ይህም ከመመዘኛው 50 በመቶ በታች እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት አንድም ተቋም ከመመዘኛው በታች አልሆነም፡፡ ይህም የጤና ቁጥጥር ባለሙያዎች ከክትትል ባሻገር ድጋፍ በማድረጋቸው የተገኘ ለውጥ ነው። በአሁኑ ወቅት በመንግሥታዊና በግል የጤና ተቋማት በተደረገው ጥናት 97 በመቶ በአረንጓዴ፣ ሶስት በመቶ በቢጫ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ብቃት ማረጋገጥና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲስተር በድሪያ ሁሴን «ባለሙያ ያልሆነ ግለሰብ ህክምና ሲሰጥና መርፌ ለመውጋት ሲዘጋጅ የተያዘበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ በዚህ ድርጊት የክሊኒኩ ፈቃድ የተሰረዘ ሲሆን፤ ግለሰቡ ክስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም መድኃኒት ቤት ውስጥ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች ረዳት በመሆን የሚሠሩባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ችግሩ መሰረታዊ መፍትሄ ለማምጣት የጤና ባለሙያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል» ብለዋል።

በጤና አገልግሎት ዘርፉ የሚታይ ህገ-ወጥነት መተኪያ የሌለውን የሰው ህይወት የሚጎዳ በመሆኑ ማረም ያስፈልጋል፡፡ ህገ-ወጥነቱን ለመቆጣጠር ሥልጣን ከተሰጠው አካል ባሻገር በጤና ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ስላለባቸው የቁጥጥር ሥራው አጋር መሆን ይኖርባቸዋል በማለት ወይዘሮ አለምፀሐይ አሳስበዋል፡፡

 

ዜና ሐተታ

ዑመር እንድሪስ – አዲስ ዘመን

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram