በመንግስት የልማት ድርጅቶች የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ የተወሰነው በቂ ዝግጅት እና ጥናት በማድረግ እንደሆነ ተገለፀ

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ እንዲተላለፉ የተወሰነው ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የእድገት ምዕራፍ ለማስቀጠል እና ከእድገት አንፃር እያጋጣሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊ ሆነ በመገኘቱ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አስታወቁ።

ይህን ውሳኔም በቂ ዝግጅት እና ጥናት በመመስረት የተላለፈ ሲሆን ፥ በመንግስት እና በድርጅት አስፈላጊው ውይይት ተካሄዶበታል ብለዋል።

የልማታዊ መንግስት ፖሊሲን ተከትለው ስኬታማ ልማት ያረጋገጡ ሀገራት ልምድ በመቀመር ይህን ውሳኔ መንግስት ማሳለፉ ተገልጿል።

ሀገራቱ በእድገታቸው ጎዳና ያጋጠማቸውን ተግዳሮት ያለፉበት ስልት ከኢትዮጵያ አንፃር ታይቶ እንደተዘጋጀ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

መንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት ያስተላለፈበት ዋና አለማ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንዲቻል ነው ብለዋል።

በዚህ ውሳኔ ከመንግስት ፓሊሲ አንፃር ትልቅ ትርጉም ያላቸው ተቋማት አብዛኛው ድርሻቸው በመንግስት እንዲቆይ ተወስኗል።

ይህም የሆነበት እነዚህ ተቋማት በልማታዊ መንግስት ማዕቀፍ እድገት ለማስቀጠል ወሳኝ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ነው ተብሏል።

ሚኒስትሩ ማሻሻያው በልማታዊ መንግስትን ፓሊሲ ማቅፍ ስር የተደረገ እንጂ የፓሊሲ ለውጥ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

የገቢያ ጉድለት በሚታይባቸው እንደ አገልግሎት፣ መሰረት ልማት እና የምርት ተቋማት ወይም የፓሊሲ ማስፈፀሚያ ናቸው ተብሎ በሚታመንባቸው እድገትን ለማረጋገጥ መንግስት ድርሻ ይኖረዋለ።

በማሳያነትም ኢትዮ-ቴሌኮም ፣ የኤሌክትሪክ አገልግለት፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ እንዲሆም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጠቀሱ ሲሆን፥ የፓሊሲ ማስፈፀሚያ በመሆናቸው አብዛኛው ድርሻቸው በመንግስት ስር ይሆናል ተብሏል።

የመንግስት የልማት ድርጂቶቹ በተለያየ ደረጃ ወደ ግል ይዞታነት ሲተላለፉ ግልፀኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ማዕከል ባደረገ እና ሞኖፖሊን በማይፈጥር መልኩ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈ እንደ መንግስት ፓሊሲ ማስፈፀሚያነነት የማይወሰዱት የባቡር፣ የስካር ማምረቻ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞታ እንዲተላለፉ ተወስኗል።

እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ ወደ ግል ይዞታነት እንዲተላለፉ የተወሰነው ለመንግስት ከፍተኛ የፋይናስ አቅም ለመፍጠር፣የኢኮኖሚውን እድገት ለማስቀጠል፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ በማሰብ ነው።

እንዲሁም ሀገሪቱ ካጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የልማታዊ መንግስት ጉዞ በተጠናከረ መልኩ ለማሰቀጠል እንደሆነም ተነግሯል።

ይህ ማሻሻያ ሀገሪቱ እያጋጠማት ካለው የኢኮኖሞ ችግር እንፃር ጠቃሚ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል።

የመንግስት እርምጃ የፋይናስና የኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በማበረታታት የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ይረዳል።

በተለይ ሀገሪቱ በበቂ ሁኔታ ለልማት ያልተጠቀመችበት የግሉ ዘርፍ ለፈጣን እድገቱ ተጨማሪ አቅም እንዲሆን ነው ተብሏል።

እነዚህ ወደ ግል ይዞታነት የሚተላለፉ ተቋማት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር መንግስት የቁጥጥር ስራ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post

%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram