በሕገወጥ መንገድ የተገኘ 520.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ አስመስለው አቅርበዋል የተባሉ ተከሳሾች በነፃ ተሰናበቱ
- ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጣለባቸው
ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተከለለና ለውጭ ዜጎች ባልተፈቀደ የንግድ ሥራ ዘርፍ ተሰማርተው፣ በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ከ520.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል አቅርበዋል ተብለው ከሦስት ዓመታት በላይ በእሥር ሆነው ሲከራከሩ የከረሙት የኢትዮጵያ፣ የስሪላንካ፣ የህንድ፣ የኒውዚላንድ፣ የጂቡቲና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዜጎች በነፃ ተሰናበቱ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ሁለት ኢትዮጵያውያን፣ አምስት የስሪላንካ ዜጎች፣ አራት የህንድ ዜጎች፣ አንድ የኒውዚላንድ ዜጋ፣ አራት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዜጎችና አንድ የጂቡቲ ዜጋ ሲሆኑ በድምሩ 17 ናቸው፡፡ የጂቡቲ ዜግነት ያላቸው ሲና መሐመድ መሐሙድ የተባሉት ተጠርጣሪ ከጅምሩ በብይን በነፃ ተሰናብተዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን 520,529,149 ብር ሕጋዊ አስመስለው አቅርበዋል የተባሉት አቶ አሽረፍ አወልና ድርጅታቸው አካፔ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና አራት የስሪላንካ ዜጎች በነፃ እንዲሰናበቱ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ችሎት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ የሰጠባቸው ተከሳሾች ሁለቱ ኢትዮጵያውያንና አራቱ ስሪላንካውያን፣ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን ሲከታተሉና ሲከራከሩ የከረሙ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊው አቶ አሽረፍ ሁለት የስሪላንካ ዜጎች የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ባልተፈቀደላቸው የንግድ ሥራ እንዲሰማሩ በማድረጋቸው ተጠያቂነትን የሚያስከትልባቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠቁሞ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ሁለቱ የስሪላንካ ዜጎችም ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ በተፈቀደ የባጃጅ ችርቻሮ ንግድ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተመዘገበው አካፔ ኢምፔክስ ደግሞ 441,409 ብር የንግድ ግብር ባለመክፈልና ገቢ በመቀነስ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ ሌሎቹ አሥር ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት የታየ በመሆኑ ሁሉም ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርድ ቤቱ የሰጠው የፍርድ መዝገብ ያሳያል፡፡ ሚስተር ቦፒ ጊድራ አጅት ኩማር ሳማራታህንና ሚስተር ኩሩፑ አራችትግዶን ኒቫልፕሪያንካ ራትናስካራ የተባሉት የስሪላንካ ዜጎች፣ በሁሉም ክስ በነፃ በመሰናበታቸው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ በመሰጠቱ፣ እንደተፈቱና ወደ አገራቸው መሄዳቸው ታውቋል፡፡ አሥር ተከሳሾች ደግሞ ክሳቸው በሌሉበት የታየ በመሆኑ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ፍርድ እንዳስታወቀው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ ያቀረበው አቶ አሽረፍ አወል፣ ወ/ሮ ሲና መሐመድ፣ አጋፔ ኢምፔክስና ሁለት የስሪላንካ ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች በሕገወጥ የተገኘ 520,529,144 ብር ሕጋዊ አስመስለው አቅርበዋል ብሏል፡፡ ገንዘቡም ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ከተሠራ ሕገወጥ ንግድ ገቢና ከግብር ስወራ ያገኙት መሆኑንም በክሱ ማስረዳቱን ጠቁሟል፡፡ 512,768,820 ብር ጠቅላላ የተሸጠ ዕቃ ዋጋ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የኦዲት ማስረጃ እንደሚገልጽ ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡ 7,760,328 ብር ደግሞ ከግብር ስወራ የተገኘ መሆኑን አክሏል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በምርመራው እንዳረጋገጠው 512,768,826 ብር የጠቅላላ ዕቃ ሽያጭ እንጂ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ድንጋጌ መሠረት በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ስለመሆኑ በዓቃቤ ሕግ በኩል የቀረበ የኦዲት ሪፖርት እንደሌለ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ከጠቅላላ ሽያጭ እንጂ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሊባል አይችልም ብሏል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሕገወጥ መንገድ በገንዘብ ስወራ ተገኝቷል ብሎ ያቀረበው የ7,318,918 ብርን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ መመርመሩን አስታውቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረበው አካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተለያዩ ባንኮች አስቀምጦት የተገኘ ገንዘብ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ የአካፔ ኢምፔክስ የካፒታል ምንጭ ሕገወጥ ስለመሆኑ በክሱ አለመግለጹን ፍርድ ቤቱ አረጋጋጦ፣ ድርጅቱ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፍ የተሰማራና ካፒታሉ በሕጋዊ መንገድ እያሳደገ መጥቶ 102,044,000 ብር ያደረሰ መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃነት ካቀረበውና ተከሳሾቹ በመከላከያ ማስረጃነት እንዲያዝላቸው ከጠቀሱት የኦዲት ሪፖርት መረዳቱን ገልጿል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሰው 17,681,833 ብር በግብር ስወራ የተገኘ ወይም ከሌላ ሒሳብ የተገኘ ነው ለማለት የሚያስችል የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ግን በክሱ እንዳብራራው ሁሉም ተከሳሾች ማለትም አቶ አወል፣ ወ/ሮ ሲና መሐመድና ሌሎቹም ተከሳሾች፣ አካፔ ኢምፔክስ፣ ዱባይ አውቶ ጋለሪ ኤልኤልሲና አውቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ኩባንያዎችን በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተከለለና ለውጭ ዜጎች ባልተፈቀደ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ከላይ የተጠቀሰውን 520.5 ሚሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ ማግኘታቸውን ማብራራቱን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ጠቁሟል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ስለገንዘቡ ሕገወጥነት ሲያብራራም 104,278,157 ብር በአካፔ ኢምፔክስ ስም፣ 199,667 ብር በአቶ አሽረፍና በባለቤታቸው ስም በተለያዩ ባንኮች የተቀመጠና ቀሪው 416,051,324 ብር ደግሞ ዝውውሩ የተደበቀ ገንዘብ መሆኑን መግለጹን ፍርድ ቤቱ በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ግብርን ባለመክፈልም በድምሩ 7,760,328 መገኘቱንም ዓቃቤ ሕግ መጥቀሱንም ፍርድ ቤቱ ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ዓቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሳቸውን የገንዘብ መጠን በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ከማለት ባለፈ፣ በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ አካፔ ኢምፔክስ ከባጃጅ ሽያጭ ውጭ በተለያዩ የንግድ ዘርፍ በአስመጪነት የተሰማራ የንግድ ድርጅት መሆኑንና እንቅስቃሴውም ጤናማ መሆኑ የተረጋገጠ ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡ ይህንንም ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው ከራሱ ማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁሟል፡፡ ካፒታሉ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመጣና ያደገ መሆኑን ተከሳሾቹ ባቀረቧቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ያረጋገጡና ክሳቸውን በተገቢው ሁኔታ መከላከል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አቶ አሽረፍ ድርጅታቸውን አካፔ ኢምፔክስን ሽፋን በማድረግ ሱሬንድራና ኢሲታ የተባሉት የስሪላንካ ዜጎች ምንም ዓይነት የፀና ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀደ የንግድ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረጋቸው አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 102(3)ን መተላለፋቸውን በመግለጽ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ሁለቱ የስሪላንካ ዜጎች የአካፔ ኢምፔክስ ተቀጣሪ ሆነው ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ነገር ግን ዜጎቹ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀደ የሥራ ዘርፍ በመሰማራት፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በመዘዋወር የባጃጅ ችርቻሮ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ የአካፔ ኢምፔክስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሽረፍና ሁለቱ የስሪሊላንካ ዜጎች አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 60(1) ሥር የተደነገገውን ተላልፈው ተገኝተዋል በማለት በአብላጫ ድምፅ ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በሐሳብ የተለዩት ዳኛ ግን ዝርዝርና ሰፊ ትንታኔ በመስጠት ሁሉም ተከሳሾች ክሳቸውን በአግባቡ ተከላክለዋል በማለት በነፃ መሰናበት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአብላጫ ድምፅ ጥፋተኛ የተባሉት አቶ አሽረፍ አወል፣ ስሪላንካውያኑ ሂትራጅግ ያሳንታና ፕላንዎታጅ አሲታ እያንዳንዳቸው የአምስት ዓመታት ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ አካፔ ኢምፔክስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ 33,000 ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ምንጭ – ሪፓርተር