fbpx

በሕዝብ ላይ መቆመር አስነዋሪ ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚታወቅባቸው ዋነኛ መለያዎቹ መካከል ለአገሩ ያለው ጥልቅ ፍቅር አንደኛው ነው፡፡ ይህ የአገር ፍቅር ስሜት ራስን በፈቃደኝነት ለመስዋዕትነት ከማቅረብ ጀምሮ፣ በልዩ ልዩ አበርክቶዎች እየተገለጸ ዘመናትን መሻገር ተችሏል፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ከማንም ጋር ተደራድሮ አያውቅም፡፡ አገሩን በክፉ የሚያዩትን ጭምር ሲፋለም ኖሯል፡፡ ለዘመናት ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ጋር እየተፋለመ እናት አገሩን ሲጠብቅ የኖረው፣ ከአገሩ በላይ ምንም የሚያስቀድመው ባለመኖሩ ነው፡፡ ይህ አስተዋይ ሕዝብ በፊትም ሆነ አሁን አገሩን የሚያየው እንደ ዓይን ብሌኑ ስለሆነ፣ አገሩን የሚነኩበትንም ሆነ ለአደጋ የሚያጋልጧትን በፍፁም አይቀበልም፡፡ ይህንን ታሪካዊና አንፀባራቂ የአገር ፍቅር ስሜት በተለያዩ ጊዜያት ለማጥፋት የተደረጉ ሙከራዎችም አልተሳኩም፡፡ ሕዝባችን በእርስ በርስ መስተጋብሩም ሆነ ከባዕዳን ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገሩ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ መረዳት ያቃታቸው ወይም የማይፈልጉ ግን ከፍላጎቱ በተቃራኒ ስህተት እየፈጸሙ ነው፡፡ ሕዝባችን በአገሩ ላይ ከሚቆምሩ የሥልጣን ጥመኞችም ሆነ የጠላት ተላላኪዎች ጋር በፍፁም አይግባባም፡፡ የሚደረጉ አጉል ሙከራዎችም ተስፋ የላቸውም፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ በፖለቲከኞች ዘንድ ሕዝብ እየተረሳ ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት ፈቃዱን መፈጸም ሲገባ፣ በሕዝብ ላይ መቆመር በስፋት የተለመደ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት በሚደረገው መሯሯጥ የአገርን ህልውና የሚጋፉ አሳዛኝ ድርጊቶች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከወቅቱ አንገብጋቢነት አንፃር እየመዘኑ ምላሽ በመስጠት አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጎዳና ማስገባት ሲገባ፣ በውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻ በመጠመድ መፋጠጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከስብሰባ ወደ ስብሰባ እየተሸጋገረ የውስጥ ደዌውን ሲያስታምም፣ ክፍተቱን ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ አገሪቱን ከቀውስ ወደ ቀውስ ለማሸጋገር እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ፡፡ ይህንን አጋጣሚ እንደ ገፀ በረከት የሚቆጥሩ ታሪካዊ ጠላቶች ደግሞ በእሳቱ ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋሉ፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያገለግሉዋቸውን ከሃዲዎች ይመለምላሉ፡፡ በዚህ መሀል ሕዝቡ ከምንም በላይ የሚወዳት አገሩ ወደማይታወቅ አቅጣጫ ትነጉድበታለች፡፡ ይህ የፖለቲካ ቁማር እየጎዳ ያለው ሕዝቡን መሆኑን ተረድቶ ከማያስፈልግ ድርጊት ለመታቀብ ጥረት ሲደረግ አይታይም፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡

አስተዋዩ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው ከማንነት ጀምሮ እስከ እምነት ያሉ ልዩነቶቹን በመከባበርና በመተሳሰብ በማቻቻል፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን ሲያስቀድም ነው፡፡ ድንበር ገፍተው የመጡ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ወኔ ሲያባርር የኖረውም፣ ከልዩነቶቹ ይልቅ አገር ለምትባለው የጋራ ቤቱ ቅድሚያ ስለሚሰጣት ነበር፡፡ አሁንስ? በተለይ አሁን ባለንበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ የአገር የጋራ ጉዳይ ወደ ጎን እየተገፋ ቡድንተኝነት የወለደው ጽንፈኝነት ውስጥ እየተገባ ነው፡፡ በተለይ ፊደል የቀሰመው የኅብረተሰብ ክፍል ከቆመለት የቡድን ዓላማ በላይ አገር መኖሯን እርግፍ አድርጎ የተወ ይመስላል፡፡ አገርን ማዕከል አድርጎ የሕዝብን የጋራ ጥቅም ከመወከል ይልቅ፣ ሥልጣንን ማዕከል ያደረገ ቡድንተኝነት ውስጥ በመዘፈቅ አገርን ማተራመስ ፋሽን ሆኗል፡፡ በሕዝብና በአገር ስም እየማሉ ከቆሙለት የጠበበ ዓላማ አልላቀቅ ያሉ እየበረከቱ ነው፡፡ ሕዝቡን በስሙ ይነግዱበታል እንጂ፣ የሚወዳትን አገሩን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት አይፈልጉም፡፡ ይልቁንም አጋጣሚውን የሥልጣን መንጠላጠያ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሕዝብ ላይ መቆመር ማለት ይኼ ነው፡፡

ለአገራቸው የሚቆረቆሩና ዘላቂ ሰላሟን የሚፈልጉ ዜጎች ከጽንፈኝነት የፀዳ ሐሳብ ሲያቀርቡ፣ ግራና ቀኝ በተሠለፉ የጽንፍ ኃይሎች ይኮረኮማሉ፡፡ አምባገነንነትን እንታገላለን እያሉ የሚመፃደቁ ጽንፈኞች ከእነሱ ጋር ያልወገነ አስተያየት መስማት አይፈልጉም፡፡ አንድ ዜጋ በአገሩ ጉዳይ ላይ የመሰለውን ሐሳብ ሲያቀርብ አማካይ የሚባል ሥፍራ እንዲኖር አይፈለግም፡፡ መደገፍ ወይም መቃወም ብቻ እንጂ ገለልተኝነት አይፈቀድም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሐሳብን በነፃነት ማቅረብ ስለማይቻል በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች ያሏቸው ዜጎች ተሸማቀው ተቀምጠዋል፡፡ ደፈር ብለው የወጡት ደግሞ በሚዘገንን ስድብ ጥጋቸውን እንዲይዙ ይደረጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ይህንን ዓይነቱን አስነዋሪ ድርጊት አይቀበልም፡፡ ምክንያቱም ሕዝባችን በየዕለት ግንኙነቱ ከቤተሰብ እስከ ጎረቤት ድረስ በነፃነት ሐሳቡን ያንሸራሽራል፡፡ ‹የመሰለውን ተናግሮ የመሸበት ማደር› ልማዱ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ በምሳሌያዊ አነጋገሮቹም ሆነ በምክሮቹ የሚያበረታታው ግልጽነትን ነው፡፡ ይህ ግልጽነቱ ደግሞ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነትና በመሳሰሉት ልዩነቶቹ ሳይገደብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን ለማጠናከር ጠቅሞታል፡፡ የዘመኑን መፋዘዝና መፈራራት እንደ ምሳሌ በማንሳት ሕዝቡ ውስጥ ግልጽነት የለም የሚባለው አባባል ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ የአገሩን ነፃነት አስከብሮ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርዓያ መሆን የቻለው፣ በአንደበቱም ሆነ በዓይኖቹ ጭምር መግባባት ስለሚችል ነበር፡፡ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይልን አከርካሪውን የሰበረ ጀግና ሕዝብ እኮ መነጋገርም መደማመጥም ይችል ነበር፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ብርቅ የሆነው በዚህ ዘመን ነው፡፡

መነጋገርና መደማመጥ ያቃታቸው የዘመኑ ፖለቲከኛ ተብዬዎች የአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መግባባት ይችላሉ? እያንዳንዱ የአገር ጉዳይ የመነታረኪያና የጠላትነት ማዳበሪያ መሆኑ የዚህ ዘመን ዓበይት ክስተት ነው፡፡ በእያንዳንዱ የአገር ጉዳይ ላይ መግባባት ለመፍጠር መነጋገር ያልቻለ ትውልድ የአገር ጠላት እየሆነ ነው፡፡ ጥቃቅኗን ጉዳይ ሳይቀር የቂም በቀልና የቁርሾ ሰለባ በማድረግ መነታረክ በተለመደባት የአሁኗ ኢትዮጵያ፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ራሳቸውን ያጀገኑ ጀብደኞች አማካይ የሚባል ሥፍራ እንዳይኖር እየተቅበዘበዙ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት ምን እንደሆነ የማይገባቸው ከጠባብ የአካካቢ ስሜት ያልተላቀቁ ወፈፌዎች በምን መመዘኛ ነው ለሕዝብ የሚጨነቁት? ለአገር የሚያስቡት? በሌላ በኩል አገር እናስተዳድራለን የሚሉ ወገኖችስ እንዴት ሆነው ነው ለሕዝብ ጥቅም እየሠራን ነው የሚሉት? መጀመሪያ አገርንና ሕዝብን ማስቀደም ሲገባ በሥልጣን ሽኩቻ መታመስ የጤና ነው? የአገር ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ሕዝብ ጭንቀት ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ከጥፋት ወጣ ብሎ ትክክለኛውን ጎዳና ለመያዝ አለመሞከር ያስነቅፋል፡፡ በታሪክ ፊትም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት በማውጣት የተሻለች አገር እንድትሆን መነሳት ሲገባ፣ ክብሪት ይዞ ነዳጅ ፍለጋ መንቀሳቀስ ሕዝብ ላይ መቆመር ነው፡፡ ሕዝብ የቁማርተኞች መቀለጃ መሆን የለበትም፡፡

ነፃነት የሚኖረው አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ የሚካሄድበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን ሲይዝ ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ በምልዓት እንዲገኙ ከአሳሪና አፋኝ አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መልዕክት አገር የሚያስተዳድሩትንም ሆነ ፖለቲካ ውስጥ አለን የሚሉ ኃይሎችን በሙሉ የሚመለከት ነው፡፡ ውስጡ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ሥፍራ የሌለው ጽንፈኛ አጋጣሚውን ካገኘ ጨቋኝ ነው የሚሆነው፡፡ ‹‹ዕብድ ቢጨምት እስከ ስድስት ሰዓት ነው›› እንደሚባለው፣ ውስጣቸው በጽንፈኝነት የተሞላ ኃይሎች በሕዝብ ስም የሚምሉት የሚፈልጉን ሥልጣን እስኪይዙ ድረስ መሆኑን መረዳት ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳ ደም የሚሸታቸውና ያገኙትን ነገር ለማውደም ወደ ኋላ የማይሉ ጽንፈኞች አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡ ይህ አደብ ሕዝብን ከማክበርና ፍላጎቱን ከማሟላት ይጀምራል፡፡ በሥልጣን ጥም የተቃጠሉ ወጣቱን ከታጠቀ ኃይል ጋር እያጋፈጡ ለሕዝብ ጥቅም ነው ሲሉ አትቀልዱ መባል አለባቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ተብሎ በሕዝብ ስም ሲቀለድም ይበቃል መባል አለበት፡፡ ይህ ኩሩ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በመጀመርያ የሚፈልገው የአገሩን ሰላም ነው፡፡ ሰላም ሲኖር ዴሞክራሲና ብልፅግና እንደሚኖር ይረዳልና፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መቆመር አይቻልም! አስነዋሪ ነው!

ምንጭ፤- ሪፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram