በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ገለፀ
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት የቀለም አብዮት መልክ እየያዘና በግልጽ ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ እየታየበት መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ገለጸ።
ሁኔታው ተቀባይነት የሌለውና መቼም ቢሆን በነውጥ፣ በአቋራጭና በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ የሚለወጥ መንግስት እንደማይኖር ነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር እና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የተናገሩት።
እነዚህ የቀለም አብዮት አራማጆች ተከታታይ ሁከቶችን በመጥራት እና በማስተባበር መንግስት ላመናቸው ትክክለኛ የህብረተሰብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳይሰጥ እና በመንግስት እና በህብረተሰቡ መካከል መቃቃር ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን ነው አቶ ሲራጅ የገለፁት።
አቶ ሲራጅ ያለፉት ቀናትን የፀጥታ ሁኔታ ሲያብራሩም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በተቋማትና ፋብሪካዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንም አንስተዋል።
በዚህም እስካሁን 17 የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ደርሷል፥ ከፀጥታ አካላቱ ላይ የመሳሪያ ነጠቃ መፈጸሙንም አብራርተዋል።
በአራት ተሽከርካሪዎች ላይ ቃጠሎና 10 ተሽከርካሪዎች ተጎድተዋል ያሉት አቶ ሲራጅ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች መቃጠላቸውንም ጠቅሰዋል።
ኮማንድ ፖስቱም በዚህ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እያከናወነ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላም የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ጠቅሰው፥ ከአዲስ አበባ-አምቦ-ነቀምት-አሶሳ መንገድ እስካሁን የትራንስፖርት አገልግሎት አለመጀመሩን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ -ወሊሶ – ጅማ መስመር ትራንስፖርት መቋረጡንም ገልፀዋል፤ በእነዚህ አካባቢዎች በቂ የፀጥታ ሃይል መመደቡን በመጥቀስ ሁኔታውን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ደምቢዶሎና ነቀምት አካባቢዎች የንግድ ቤቶች በሚደርስባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ መዘጋታቸውንም አስታውቀዋል።
ከአዋጁ መታወጅ በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ እልባት ለመስጠትም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
ህብረተሰቡም ለኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ኮማንድ ፖስቱ ጥሪ አቅርቧል።
ኮማንድ ፖስቱ ህብረተሰቡ 012- 552-70 03 እና 012- 551- 14 29 የስልክ መስመሮች በመደወል አስፈላጊውን ጥቆማ መስጠት ይችላል ነው ያለው።
ኤፍ ቢ ሲ