fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ቃለ-ምልልስ ከዮናታን ተስፋዬ ጋር

ከታህሳስ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ዝዋይ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት ተለቅቀዋል። አቶ ዮናታን ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ዛሬ የተፈቱት ድንገት ሳያስቡት ነው።

የእስር ጊዜያቸውን ለመጨረስ አንድ ወር ከ18 ቀን ብቻ ይቀራቸው እንደነበር የተናገሩት አቶ ዮናታን ዛሬ በድንገት መለቀቃቸውን ገልጸዋል። ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተዘጋበት ቀን ከእስር በመውጣታቸው መቸገራቸውን አስረድተዋል። ቀደም ሲል በርካታ እሥረኞች በተለቀቁበት ወቅት የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፈርሙ ቀርቦላቸው እንደነበር አስታውሰው አልፈርምም በማለታቸው እዚያው እንዲቆዩ መደረጉን ተናግረዋል።

ወጣቱ ፖለቲከኛ የታሰሩት ከሶስት አመት ገደማ በፊት የኦሮሞ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ በወሩ አካባቢ ነበር። በግል የፌስቡክ ገጻቸው በፃፏቸው አስተያየቶች ሽብርን የማበረታታት ክስ ቀርቦባቸው የነበረው አቶ ዮናታን በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አባል ናቸው በሚልም ተወንጅለዋል።
የቀረበባቸውን ውንጀላዎች ተቃውመው በፍርድ ቤት ሲከራከሩ የነበሩት ፖለቲከኛው በወቅቱ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩትን የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ዶ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በመከላከያ ምሥክርነት ጠርተውም ነበር።

አወዛጋቢውን የጸረ-ሽብር አዋጅ ተላልፈዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ሲመለከት የቆየው የከፍተኛው ፍርድ ቤት አቶ ዮናታን በፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሯቸው አስተያየቶች በመንግሥት ሽብርተኛ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም ኹከት የመቀስቀስ አቅም አላቸው ማለቱ አይዘነጋም። የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈው ፍርድ ቤቱ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር እንደፈረደባቸውም ይታወሳል። አቶ ዮናታን በውሳኔው ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያሉ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ክሳቸውን ከሽብር ወደ መደበኛ የወንጀል ክስ ቀይሮ የእስር ጊዜያቸውን ወደ ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ቀንሶላቸዋል።

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ – DW Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram