fbpx

ሽው ወደ አሥመራ

እናትና ልጅ በአሥመራ ሲገናኙ ፤

ሀምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ልዩ ቀን ናት። ለነገሩ ባለፉት ሳምንታትም በርካታ ልዩ ቀናትን አሳልፈናል። ይህች ቀን ግን ብዙዎች ሲናፍቋት እንዲሁም ሲዘጋጁባት የነበረች በመሆኗ ልዩ ተብላለች። ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 465 መንገደኞችን አሳፍሮ ጉዞውን ወደ አሥመራ በማድረግ በሰላም መድረሱ ታውቋል።

«ትምህርቴን አጠናቅቄ በረራ የጀመርኩት ከአዲስ አበባ አሥመራ በሚደረግ ጉዞ ላይ ነው፤ ከቤቴ ወጥቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆቴል ያደርኩትም አሥመራ ላይ ነው፤ ስለዚህ ለእኔ አሥመራ ልዩ ትዝታ ያላት ከተማ ናት›› ነበር ያሉት ከ20 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን በረራ ከአዲስ አበባ አሥመራ ለማድረግ በከፍተኛ ዝግጅትና ጉጉት ላይ የነበሩት ካፒቴን ዮሴፍ ሀይሉ።

ካፒቴን ዮሴፍ አዳዲስ መዳረሻዎች ሲከፈቱ የማብረር ዕድል አግኝተዋል፡፡ የዛሬው ግን ከሌላው ጊዜ እጅግ ለየት እንዳለባቸው ይናገራሉ። በተለይ ከበርካታ የጦርነትና የመኮራረፍ ጊዜ በኋላ በተገኘው ሰላም አማካኝነት የመጀመሪያ በረራ ወደ አሥመራ ላደርግ በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል በማለት ይናገራሉ።

ሌላው በአየር መንገዱ ለ34 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ሲሳይ ግርማ አሥመራ ላይ በሥራ ምክንያት ስድስት ወራት ቆይተዋል፡፡ በእነዚያ ስድስት ወራት ውስጥ ብዙ የሚያስታውሷቸው ብሎም ደስ የሚሏቸውን ጊዜያት ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ ያኔ ለሥራ አሥመራ በሰላም ነበር የሄዱት፡፡ ኋላ ላይ ግን ጦርነት ተቀስቅሶ በከፍተኛ ስጋትና ችግር መመለሳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከ 20 ዓመታት በኋላ የሰላም ብስራት ተበስሮ መንገዱም ሰላማዊ ሆኖ ዳግም ለመሄድ መቻላቸው ደስታን እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል።
የዮድ አቢሲኒያ የባሕል ምግብ ቤት መሥራችና ባለቤት አቶ ትዛዙ ኮሬ፤ የባሕል የሙዚቃ ቡድናቸውን ይዘው እንደሚሄዱና ቡድኑም አሥመራ ላይ የሙዚቃ ዝግጅት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያው ተጓዥ መሆናቸውና ከአሁን ቀደም የሚያውቋትን አሥመራን ከ20 ዓመት በኋላ ሊያዩዋት መሆኑም እጅግ እንዳስደሰታቸው ነው የተናገሩት።

ከሥራቸው አንጻር ይህ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጀመሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ በበኩላቸው በሙያቸው ይህንን ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለማከናወን እቅድ ይዘው ለመንቀሳቀስ ጉጉት እንዳደረባቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ የዛሬው ቀን በኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪክ ውስጥ አዲስ ቀን ነው ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ላለፉት 20 ዓመታት ድንበሩ፣ የአየር የየብስ እንዲሁም የስልክና ሌሎች መገናኛ መንገዶች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ይህ ታሪክ ተቀይሮ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከአዲስ አበባ አሥመራ በቀን ሁለት ጊዜ በረራዎችን ሊያደርግ ዝግጅቱን ያጠናቀቀበት ወቅት ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ፤ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለምንም ገደብ በአየር ይገናኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከሁለቱ አገራት በላይ በተለያዩ ስፍራዎች ያሉ ኤርትራውያን ከዚህ ቀደም ወደ አገራቸው ለመግባት የሚያደርጉትን ረጅምና ብዙ ወጪን የሚጠይቅ ጉዞ ያስቀራል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል አቋርጠው በቀላሉ አገራቸው ለመግባት ያስችላቸዋል በማለት ዘርፈ ብዙ ጥቅሙን አብራርተዋል።

ወደ አሥመራ የሚደረገውን የመጀመሪያውን በረራ እየመሩ የሄዱት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ይህ ቀን ታሪካዊ ከመሆኑም በላይ እርሳቸውም ይህንን ቡድን እየመሩ አሥመራ የመሄድን ዕድል በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም አየር መንገዱ የሁለቱን አገራት የተነፋፈቁ ሕዝቦች በማገናኘት ብሎም ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያላቸውን ሥራዎች በማከናወን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእቅድ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል የኤርትራን አየር መንገድ 20 በመቶ ድርሻ መግዛት የሚገኝበት መሆኑም በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ዜና ሐተታ
እፀገነት አክሊሉ – የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram