fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ሰውነት የሚያስፈልገውን በቂ ሃይልና ብርታት ለማግኘት

ድካምና የሰውነት ብርታት ማጣት በስራ አልያም ደግሞ በሌሎች ምክንያት ሊከሰት ይችላል።

ምናልባትም በቂ እንቅልፍ አለማግኘት፣ ከስራ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር መጨናነቅ እንዲሁም ስር የሰደደ የጤና እክል ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይነገራል።

የጤና ባለሙያዎችም ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰውነትዎ በቂ ሃይል በማግኘት ብርቱና ንቁ እንዲሆኑ የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ።

አመጋገብ፦ አመጋገብ ሰውነት የሚፈልገውን በቂና ተመጣጣኝ ሃይል ያገኝ ዘንድ እጅጉን እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ጤናማና ለሰውነት ግንባታ የሚረዱና ተመጣጣኝ ምግቦችን መመገብ እንደሚገባም ይመክራሉ።

ሴት ልጅ በቀን ከ1 ሺህ 600 እስከ 2 ሺህ 400 እንዲሁም ወንድ ደግሞ ከ2 እስከ 3 ሺህ ኪሎ ካሎሪ መውሰድ እንደሚገባቸውም ነው የሚመክሩት።

ሃይል ሰጭ ምግቦችን መመገብም ለዚህ ወሳኙ ነገር ነው፤ ጥራጥሬ፣ ለውዝ፣ ወይን፣ አፕል፣ ብርቱካን፣ ኮክ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ እና እንደ መንደሪን ያሉ ፍራፍሬዎችን መመገብ።

ከዚህ ባለፈም የአሰር (ፋይበር) ይዘታቸው ከፍ ያሉ እንደ አተርና ባቄላ እንዲሁም አረንጓዴ የአትክልት ዘሮችን ማዘውተር።

ባለሙያዎች ከዚህ ጋር ተያይዞ ነቃ ለማለት የሚወሰድ ቡና ምናልባት ረፋድ ከ4 ሰዓት አልያም ከቀትር በኋላ 9 ሰዓት አካባቢ ቢሆን እንደሚመረጥ ያስረዳሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ ምንም ያክል የተጣበበ ጊዜ ቢኖርዎትም በጣም በጥቂቱም ቢሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን ይመክራሉ።

ምናልባትም ማለዳ ላይ ተነስተው የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ጫና ያልበዛበት ሩጫ መሮጥ፣ በጣም ቀላል የሚባሉ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች በሳምንት አምስት ወይም ስድስት ቀን ለግማሽ ሰዓት ያህል መከወን።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ድካም ሳይሆን ለሰውነት ብርታትን ያመጣል፤ ሰውነት የኦክስጅን የመሸከም አቅሙን እንዲጨምርም ይረዳዋል።

እንቅስቃሴ ባደረጉ ቁጥርም ሰውነት የበለጠ እንዲነቃቃና ሃይል እንዲያገኝ የሚረዳውን ሆርሞን በብዛት እንዲያመነጭም ያደርገዋል።

ተመስጦ ማድረግ፦ ካለዎት ጊዜ ላይ የተወሰነውን ጊዜ እንደ ዮጋ ላሉ የተመስጦ እንቅስቃሴዎች መጠቀምም ሰውነት ብርታትና ሃይል እንዲያገኝ ይረዳዋል።

ይህንም ከቻሉ በቀን ለግማሽ ሰዓት ያክል ቢጠቀሙ በስራ ጫና ሊከሰት የሚችልን የስሜት መቀያየርና ድብርት በማስወገድ ሰውነት ብርታቱን እንዳያጣ ይረዳዋል።

የስራ ጫናን መቀነስ፦ ምናልባት ካለብን ሃላፊነት አንጻር ይህን ማድረጉ ከባድ ቢመስልም እንኳን ስራዎችን እወጣለሁ በሚል ራስ ላይ የበዛ ጫና መፍጠሩ አግባብ አይደለም።

የስነ ልቦና ባለሙያዎችም የቱንም ያክል ቀላል ቢሆን እንኳን ስራን ብቻን ለመከወን ጊዜ ከማጣበብና ከመጣደፍ ለሌሎች ማጋራትና ጫናን በተወሰነ ደረጃ መቀነስን ይመክራሉ።

እናም በተቻለ መጠን አስቸኳይም ቢሆን አሁኑኑ ካልሆነ በሚል ራስ ላይ የበዛ ጫና መፍጠሩ ፍጹም አግባብ አይደለምና የተወሰኑ ሃላፊነቶችን ለሌሎች በማጋራት ራስዎ ላይ ጫናን ይቀንሱ።

ይህን ሲያደርጉ አዕምሮን ከልክ በላይ በማስጨነቅ ላልተፈለገ ጭንቀት ይዳረጋሉ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ሰውነት ከልክ በላይ እንዲደክም ያደርገዋልና ከዚህ ይታቀቡ መልዕክታቸው ነው።

በቂ እንቅልፍ መተኛት፦ ብዙም ልብ የማይባል ግን ለሰውነት ብርታት እንዲያገኝም ሆነ ለመላው ጤንነትዎ ወሳኝና አስፈላጊው ነገር በቂ እንቅልፍ ማግኘት ነው።

ምሽቱን በቂ እንቅልፍ አግኝተው ካደሩ በቀጣዩ ቀን ሰውነት የተሟላ ብርታትና ሃይሉን እንዲያገኝ ያደርገዋል።

ለዚህ ደግሞ በቀን ከ7 እስከ 9 ሰዓት መተኛት አስፈላጊ መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ከዚህ ባለፈ ግን ዘወትር ተመሳሳይ የመኝታ ሰዓትን ማስለመድና በዚያው ሰዓት መተኛት መቻል።

በመኝታ ሰዓት አካባቢ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን አለመጠቀምና አነቃቂ ነገሮችን አለመውሰድም ለዚህ ይረዳል ይላሉ ባለሙያዎች።

ከዚህ ባለፈ ግን ሲጋራና አልኮል መቀነስ፣ ጭንቀትን ማስወገድ፣ በቂ ውሃ መጠጣትና ስኳር ገበታ ላይ አለማብዛትም ለዚህ ይረዳሉና ይጠቀሙባቸው።

 

ምንጭ፦ medicalnewstoday.com

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram