fbpx
AMHARIC

”ምነው ባይኔ መጣህ!” በዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ

“ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ የሚከተለውን መልዕክት ልኳል በትዕግስት እንድታነቡለት አደራ እንላለን”
በቅርቡ ከእህቴ ከቤቲ ታፈሰ ጋ ቃለ መጠይቅ አደረኩኝ፡፡ ቃለ-መጠይቁ ከወጣ ሳምንት ባይሞላዉም በጣም Aነጋጋሪ እንደሆነ ማስተዋል ችያለሁ፡፡ የቪዲዮውን መለቀቅ ተከትሎ ብዙ ጽሁፎችና የተንቀሳቃሸ ምስል መልእክቶች ወጥተዋል፡፡ ሁሉንም ማየትና ማንበብ ባልችልም (ከብዛታቸው የተነሳ) የተወሰኑትን ግን በጥሞና ማንበብና ማየት ችያለሁ፡፡ በቃለ-መጠይቁ ላይ በተነሱ ሀሳቦች ላይ ደግሞም በእኔ ህይወት ዙሪያ ብዙ ሲባል አየሁ፡፡ ብዙ ሰዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች እንዳላቸው አስተዋልኩ፡፡ ስለዚህም አንዳንዶቹን መመለስ ህዝብን ማክበር ነው ብዬ ስላመንኩ የሚቀጠሉትን ነጥቦች በፍፁም ግልፅነት ለማስረዳት ወደድኩኝ፡፡

1. እኔና አስቴር ደምሴ፡ Aስቴር ደምሴ የቀድሞ ባለቤቴ ነች፡፡ እድሜዬ 27 Aመት… በጌታ ቤት ደግሞ የ 6 ወር ክርስትያን ሆኜ ነው የተገናኘነው፡፡ የቀድሞው የላይቤርያ ፕሬዚደንት ሳሙኤል ዶ ባለቤት ነበረች፡፡ ደም ግባት ያላት ቆንጆ ሴት ናት፡፡ እወዳት ነበር! ሚያዝያ 1987 ተገኛኝተን በወርሀ ጥቅምት 1988 ተጋባን፡፡ በድምሩ አብረን ያሳለፍነው 7 ወራቶችን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ተለያየን ልጆች አልወለድንም፡፡ አሰቴር በአሁኑ ሰአት በአሜሪካ ከሚገኙ ታላላቅ ኢትዮጵያዊ ሚሊየነሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ በሰላምና በደሰታ ኑሮዋን እየኖረች ትገኛለች፡፡ እንድ ቀን ህዝብ ፊት ቀርባ ምንም በደል እንዳላደረኩባት ትመሰክራለች ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

2. እኔና ሶፍያ ሽባባው፡ ሶፊም ረጅም ደርባባ ቆንጆ ሴት ናት፡፡ ድንቅ ዘማሪ! በሚያዝያ 1999 ዓ/ም ተገናኝተን በወርሀ መስከረም 2000 ዓ/ም ተጋባን፡፡ ሁለት ሴት ልጆች ወልደን አሳደግን፡፡ ትዳራችን ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩት ቃለ-መጠይቁ ላይ እንደተናገርኩት፡፡ እሷንም እንደ ባለቤቴ በጣም እወዳት ነበር፡፡ ሶፊ በዚህ ትዳር ብዙ ተጎዳችብኝ፡፡ ሁኔታዎች እንጂ እኔ ጎድቻታለሁ ብዬ ግን አላምንም፡፡ የዛሬ ሶስት አመት ከሶፊ ጋ መለያየት ጀምርን፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ በAንዳንድ ምክንያቶች በህግ ተለያየን፡፡ በቃ! የተደበቀ ሚስጥር የለም! በአሁኑ ሰአት ሶፊ ጌታን እያገለገለች ነው፡፡ ቻግኒ ኮፊ የሚባል ቆንጆ ካፌ ከፍታ ትሰራለች፡፡ ጎበዝ የስራ ሰውም ነች፡፡ ሌሎች ስራዎችንም ለመጀመር እየተዘጋጀች ነው፡፡ ካፌዋ ከጃክሮስ ቤቶች አለፍ ብሎ ፊጋ የሚባለው ሰፈር አካባቢ ነው፡፡ ሔዳችሁ እንደውም ተጋበዙላት፡፡ እምር ድምቅ እንዳለች ታገኟታላችሁ፡፡ አልተንከራተተችም! አልተጎሳቆለችም! በእኔና በልጆቼ እናት በሶፊ መካከል ጠብም፣ ቂምም፣ ጭቅጭቅም የለም፡፡ እንደዋወላለን፣ እናወራለን፣ ልጆቻችንን እንቀባበላለን፡፡ ያለፈውን ነገር ግን ዘግተናል!

3. እኔና ትዳር፡ ሁለት ጊዜ አግብቼ ሁለት ጊዜ ከፈረሰብኝ ችግሩ ከእኔ ነው ማለት አይደል? በትዳር ጉዳይ ምሳሌ መሆን ስላልቻልኩ እንዴት አዝናለሁ መሰላችሁ! ትዳር ክቡር ነው፡፡ ማንም መፋታት የለበትም፡፡ ባጋጣሚ ከፈታም መልሶ ባያገባ ጥሩ ነው፡፡ ቃሉ መቼም ለእኔ ተብሎ አይቀየርም፡፡ ከዚህ በኋላስ? ከዚህ በኋላማ በቃ! እኔ የትኛዋንም ሴት አላጭም አላገባም መቼም መቼም ቢሆን ትዳር ከእንግዲህ ለእኔ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፀጋውን አብዝቶልኛል፡፡ ስለዚህ የትዳር ጉዳይ በእኔ ዘንድ ፈፅሞ ዝግ ነው ማለት ነው፡፡

4. እኔና ልጆቼ፡ አሜን ወዳጄነህና ግሬስ ወዳጄነህ ይባላሉ ልጆቼ፡፡ በዚህ ምድር ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ከልኡል እግዚአብሔር የተሰጡኝ ስጦታዎቼ ናቸው፡፡ አሁን እየኖርን ያለነው እንደዚህ ነው፡፡ ጠዋት እነሳና ልጆቼን ወደ ት/ቤት እወስዳቸዋለሁ፡፡ እየዘመርን… እየፀለይን እንሔዳለን፡፡ 11 ሰዓት ሲሆን ከት/ቤት አወጣቸዋለሁ፡፡ እኔ ቤት እንገባለን፡፡ ቤቱ ኪራይ ነው አፓርትመንት፡፡ እዛ እንገባና ለእነርሱ መክሰስ ለእኔ ቡና አዘጋጃለሁ፡፡ ከዚያም ት/ቤት የተሰጣቸውን የቤት ስራ እንሰራለን፡፡ ከጨረስን በኋላ እንጫወታለን እንስቃለን፡፡ ማታ ሁለት ሰዓት ሲሆን ወደሚወዷት እናታቸው እወስዳቸለሁ፡፡ ቤታችን ቅርብ ለቅርብ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ መልካም ቲዩብ የተባለ ገፅ እኔ ልጆቼን እንደተውኩ ጭራሹኑ እንደማልደውልላቸው አድርጎ ያወጣው ፅሁፍ ልቤን ሰብሮታል! በጣም አዝኛለሁ! ምነው ወንድሜ እንደሌሎቹ እኔን መስደብ ስትችል ለምን በልጆቼ መጣህ? በዚህ አለም ያሉኝ ሀብቶቼኮ እነርሱ ናቸው! ብቸኛ ጓደኞቼኮ እነርሱ ናቸው! የአይን ማረፊያዎቼ መፅናኛዎቼኮ እነርሱ ናቸው! ለምን ባይኖቼ መጣህ? ትእዛዝ የሰጡህ አለቆችህስ ቢሆኑ ይህን ያህል እንዴት ይጨክናሉ? ‹‹ምነው ወዳጄ ምነው!›› አለ ሀበሻ! ይህንን የተናገርኩትን ከልጆቼ ጋ ያለኝን የየቀኑ ውሎ የሚጠራጠር ሰው ካለ ሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ የሚባለው የረር አካባቢ ያለው ት/ቤት ይሒድ፡፡ ጥበቃውን፣ አስተማሪዎቹን፣ ዳይሬክተሩን ይጠይቅ፡፡ ወይም 11 ሰአት ላይ ት/ቤቱ ጋ እኔን ይጠብቀኝ፡፡ እንደውም ልጆቼን ስወስድ አንዳንዴ የምገዛላቸውን ቦንቦሊኖ እጋብዘዋለሁ፡፡

5. እኔና ቤቲ ታፈሰ የዛሬ 7 Aመት አካባቢ ነው ያወኳት ቤቲን፡፡ እጅግ በጣም የምታስገርመኝ ልጅ ናት፡፡ ከእድሜዋ በላይ የሆነ እውቀት አላት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ በመስማት የምደነቅባቸው ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ አንዱ ወንድወሰን ይባላል ሁለተኛዋ ብታምኑም ባታምኑም ቤቲ ታፈሰ ነች፡፡ እርሷም በታሪክ አጋጣሚ ትዳርዋ ፈርሶባትል፡፡ ቀረብ ብሎ ላያት ጠንካራ ሴት ነገር ግን የምታስገርም የፍቅር ሴት ነች፡፡ የፕሮግራሟ ይዘት የ ቢቢሲው ጋዜጠኛ ሲቲቨን ሳከር እንደሚያቀርበው ሀርድ ቶክ አይነት ነው፡፡ በጣም ከባባድ ጥያቄዎችን ትጠይቃለች፡፡ በዚህም ብዙ ሰው እንደሚናደድባት አውቃለሁ፡፡ አቤት የምታልፍበትን መከራ ብታዩላት አቤት ስታለቅስ ብታይዋት በእውነት ትራሩላት ነበር፡፡ የምትወዷትም ብዙዎች እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ‹‹አንቺ ጀግና ነሽ›› ከማለት ያለፈ በኑሮዋ አግዛችኋት አታውቁም፡፡ እባካችሁ እስቲ ባርኳት፡፡ ከእኔ ጋ ባደረገችው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ሰውዬው ምን አስነክቶሽ ነው ለስላሳ የሆንሽው… ጠንካራ ጥያቄዎች አልጠየቅሽውም›› ብለው ወዳጆቿ እንደወቀሷት ሰምቼያለሁ፡፡ የተመካከርነው ነገር አልነበረም፡፡ እንዲሁ ፀልየን ነው የገባነው፡፡ ምናልባት ሌላ ጊዜ ያላችሁን ጥያቄ በመሉ ከእናንተም ቢሆን ተቀብላ እንድትጠይቀኝ ይሆናል፡፡

6. እኔና ቅድስት ማርያም፡ ቅድስት ማርያም ለእኔ እናቴ ነች! እመቤቴም ነች! እጅግ በጣም እወዳታለሁ አከብራታለሁ! ይህ ደግሞ ጥፋት አይመስለኝም፡፡ እንደውም ድንግል ማርያምን መውደድና ማክበር ልክ ካልሆነ ልክ መሆን አልፈልግም! ቅድስት ማርያም ቅድስት ብፅእት ንፅህት ናት፡፡ ትውልድ ሁሉ ብፅእት ያሉኛል ብላለች እኔም እነሆ ብፅእት የተባረክሽ ነሽ! ብያታለሁ፡፡ ይህ ወንጌልን መስበክ ይከለክላል? በፍፁም! ልክ እንደዚሁ ስለወንጌል የታረዱትን በዘይት ተጠብሰው የሞቱትን ስለጌታ ኢየሱስ በድንጋይ ተወግረው አንገታቸው ተቀልቶ የሞቱትን ግን በጌታ ዘንድ ህያው የሆኑትን ፃድቃን አባቶችንና እናቶችን እወዳቸዋለሁ አከብራቸውማለሁ! ቅዱሳን መላእክቱ ወዳጆቼ ናቸው! እወዳቸዋለሁ አከብራቸዋለሁ! ይህን ማድረጌ የወንጌል እንቅፋት ነው? በፍፁም አይደለም!

7. እኔና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ! አንዳንድ ሰዎች እንደዚህ ይላሉ፡፡ ‹‹የቤተክርስትያንን ታሪክ አታጥና ካጠናህ ግን ኦርቶዶክስ ትሆናለህ!›› ይላሉ፡፡ ክርስትናን በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ያቆየልን ማነው? ባፕቲስት? ሜቶዲስት? ቃለህይወት? ወይስ ሙሉወንጌል ? ኦርቶዶክስ አይደለችምን?! ፕሮቴስታንቲዝም በኢትዮጵያ ከተስፋፋ 100 Aመት አልሞላውም፡፡ ታዲያ ይህችን እናት ቤተ-ክርስትያንን ባከብራትና ያሏትን መልካም ነገሮች ብናገር ይሔን ያህል ያስቆጣል? ይህን ያህል ያናድዳል? ቆብና ቀሚስ ለብሳችሁ ኦርቶዶክስን የምትሳደቡ አገልጋዮች ለምን መለያ ቆቡንና ልብሱን አታወልቁም? ደግሞስ ‹‹ኦርቶዶክሶችን ኢየሱስን አታውቁም ማለት በደል ነው!›› ብዬ መናገሬ ይሄን ያህል ያስጮሀል? በእውነት ተገርሜያለሁ! ሁሉም አብያተክርስትያነት ለዘላለም ይኑሩ! Oርቶዶክስ ተዋህዶም ለዘላለም ትኑር!

8. እኔና ኤኪውሜኒዝም ኤኪውሜኒዝም ማለት በምድር ባለው የክርስቶስ አካል ማለትም በአብያተ-ክርስትያነት በOርቶዶክስ፣ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት መካከል የተሸለ መከባበርና መግባባት እዲኖር ጥረት የሚያደርግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ Ecumenism refers to efforts by Christians of different traditions to develop closer relationships and better understanding. ኤኪውሜኒዝም በAለም Aቀፍ ደረጃ ያሉ ክርስትያኖች አንድነትና ትብብር እዲኖራቸው የሚደክም እንቅስቃሴ ነው፡፡ Ecumenism is the movement or tendency toward worldwide Christian unity or cooperation.ኤኪውሜኒዝም ማለት እንዲህ አይነቱ መግባባትና መከባበር ማለት ነው እንጂ አንዳንዶች እንዳሉት ሀይማኖቶችን አንድ ላይ ጨፍልቆ ሌላ አንድ ሀይማኖት መፍጠር አይደለም፡፡ ምነው ወንድሞቼ ቢያንስ ጉግልን እንኳን አትጠይቁም? ይህንን መግባባት፣ መከባበር፣ መተባበር ለማጠንከር የሚደረጉ ስብሰባዎች ደግሞ ኤኪውሜኒካል ካውንስልስ (Ecumenical Councils) ይባላሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ኤኪውሜኪካል ነኝ ስል ይህንን ጥረት ከሚያደርጉ ወገን ነኝ ማለት ነው እንጂ አዲስ ሀይማኖት ወደ ኢትዮጵያ አመጣለሁ ማለት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ሃይማኖቶችን አንድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ማንም ይህንን ማድረግ አይችልም! ይህንን ማድረግ የሚችለው ሀሰተኛው ክርስቶስ ሲመጣ ብቻ ነው፡፡ ስሜን ከእርሱ ጋ ያነሳችሁ ወንድሞቼ እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ፡፡ ከተመሰረተው በቀር ማንም አዲስ መሰረትን ሊመሰርት አይችልም! እኔ አዲስ ሀይማኖት አላመጣሁም! ፕሮቴስታንት ግን አይደለሁም! ክርስትያን ነኘ!

9. እኔና አስተያየት ሰጪዎች፡ አንድ እሁድ ፓሰተር ሀልፌክማን የተባለ ስዊድናዊ ሰባኪ በጉባኤው ፊት ቆመና እንዲህ አለ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እኔና ባለቤቴ ሮማን ካቶሊክ ነን!›› ይህንን ብሎ የተደናገጠውን ጉባኤ ተሰናብቶ ወጣ፡፡ Christianity in Chrisis የተባለውን መፀሀፍ የፃፈው ሀንክ ሀኒግራፍ በይፋ ኦርቶዶክስ ሆኖ ተጠመቀ፡፡ እነዚህ ሰዎች የወሰኑትን ውሳኔ አከብራለሁ፡፡ እኔ ግን እንዲህ አላደረኩም፡፡ ማድረግ ቢያስፈልገኝ ያመንኩበትን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማልል ሰው ነኝ፡፡ በቃ ክርስትያን ነኝ! ከሁሉም መልካም የሆነውን የምቀበል ክርስትያን! ቃለ-መጠይቁ ከወጣ በኋላ አሰተያየት የሰጣችሁ ሁሉ መልካም አደረጋችሁ! እግዚአብሔር ይባርካችሁ! የምትሳደቡ ሰዎች ግን ለምን ትሳደባለችሁ? ህዝብም ቢሆን እኮ ይታዘባችኋል፡፡ የተነሱ ሀሳቦችን እንደልብ መተቸት ጥሩ ነው፡፡ እንወያይ፣ ፓኔል ዲስከሽኖች እየተዘጋጁ እንከራከር፣ ሀሳባችንን እናፋጭ እኛ ግን አንጣላ! ምን በወጣንና እንጣላለን፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች ቅድም ካነሳሁት በልጆቼ ከመጣብኝ ሰው በስተቀር በማንም አላዘንኩም፡፡ በተንቀሳቃሽ ምስል ከተላለፉት መልእክቶች ሙሉው የሰማሁት አንዲት ቀይ ድምቡሽቡሽ ያለች ልጅ ያስተላለፈችውን ነው፡፡ ‹‹ዶ/ር ወዳጄነህ በጣም ነው የምንወድህ! በጣም ነው የምናከብርህ! ok!›› እያለች ልክ ልኬን ነገረችኝ፡፡ እግዚአብሔር ያሳድግልኝ የኔ ልጅ! በተረፈ አሁንም አሰተያየት መስጠት መወያየት ይቻላልና ቀጥሉበት፡፡

10. እኔና አግልግሎት፡ Aሁን እንግዲህ እኔ ከአገልግሎት ውጪ ሆንኩ አይደል? ብዙ እንከን የሌለባቸው አገልጋዮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እነርሱ ህዝቡን ስለሚያገለግሉ የእኔ ከሜዳ መውጣት ማንንም አይጎዳም ምንም አያሳስብም፡፡ ግን ግን ይሄ እግዚአብሔር በተሰበረ እቃ ይሰራል አሉ! አገለግላለሁ በጣም ነው የማገለግለው፡፡ ራሴን ለልኡል እግዚአብሔር አቀርባለሁ፡፡ እርሱም የወደደውን ያደርጋል እንደውም በአለም ዙሪያ የሚያደርገው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ምህረቱ ለዘላለም ነውና! ምስጋና፡ ለፀለያችሁልኝና ለምትፀልዩልኝ ሁሉ ይሁን፡፡ በተለይ በጣም የምወድሽ እህቴ ገጣሚና ተዋናይት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፀዲዬ የድሮም ያሁንም ወዳጄ ፀዲ ሞገስ! በእኔ ምክንያት ታመምሽ አሉኝ፡፡ አይዞሽ አንድ ሚሊዮን ስድብ እኔን አይቀብረኝም፡፡ በጣም እወድሻለሁ! በጣም አከብርሻለሁ! እግዚአብሔር ልጆችሽን፣ ትዳርሽን፣ ስራሽን አገልግሎትሽን ይባርክ! ያነበባችሁትን ሁሉ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! ሌሎችም ሀሳቤን እንዲረዱልኝ ሼር አድርጉልኝ፡፡ አመሰግናለሁ!

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram