fbpx
AMHARIC

“ሚስት ላገኝ ነው መሰለኝ…” ኤፍሬም እንዳለ

“ሚስት ላገኝ ነው መሰለኝ…”

“–ልክ ነዋ… እዚህ አገር በመግዛትና በማስተዳደር መካከል ያለው ስስ መስመር ተፍቋላ! እንዲህ ሆኖ ታዲያ ፈገግ ማለት ወይም ዘና ማለት ከየት ይምጣ!… ትልቅ ወንበር ላይ መቀመጥ ‘ለማስተዳደር’ እንጂ ‘ለመግዛት’ እንዳልሆነ እውቀቱን ይግለጽላቸውማ!–”
ኤፍሬም እንዳለ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… አቴዝ ብቻውን ለምንድነው የመጣው! አሀ…ባህርንም እንፈልጋታለና! የእሷ አይነት የዋሆች እጥረት እየገጠመን ነዋ! ደግሞ ህጋዊ ባለቤቱ ነች ይሉ የለ! የእኛዎቹስ ወደ ቱርክ ምናምን ሄደው፣ “እንትን የሚባለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የተጫወተው እንትና የሚባለው ተዋናይ በእንትን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ዝግጅት ያቀርባል” የሚባልላቸው መቼ ነው፡፡ በሁሉም ነገር ተቀባይ ብቻ ሆነን ልንቀር ነው ማለት ነው!

እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የዚህ አገር ፖለቲከኞች ወይም “ፖለቲከኞች ነን” የሚሉ፣ ስታንድአፕ ኮሜዲ ምናምን አይተው አያውቁም እንዴ! አሀ… ፈገግታ የሚባል ነገር በአራት ዓመት አንዴ የሚጎበኛቸው ነዋ የሚመስለው! ‘ሴንስ ኦፍ ሂዩመር’ ምናምን ብሎ ነገር የለም ማለት ነው?! አለ አይደል…“ለሀበሻ ጥርስ አሳይተውት…” አይነት ነገር ይመስላል። ፈገግታ ማሳየት በራስ የመተማመን ሳይሆን የደካማነት ምልክት የሆነ ይመስል፡፡ ልክ ነዋ… እዚህ አገር በመግዛትና በማስተዳደር መካከል ያለው ስስ መስመር ተፍቋላ! እንዲህ ሆኖ ታዲያ ፈገግ ማለት፣ ዘና ማለት ከየት ይምጣ!… ትልቅ ወንበር ላይ መቀመጥ ‘ለማስተዳደር’ እንጂ ‘ለመግዛት’ እንዳልሆነ እውቀቱን ይግለጽላቸውማ!

ደንብ ማስከበሩ በየሜዳው ህገ ወጥ የሚሏቸውን የጎዳና ነጋዴዎችን እቃ በስነስርአት እንዲሰበስቡ ከማድረግ ይልቅ በእርግጫ የሚበትነው፣ ያቺ ‘የገዥነት’ ነገር በስሱም ቢሆን ስላለች ነው፡፡ ዋና ሥራ እስፈጻሚው፣ የበታቹን እንትን እንደነካው እንጨት የሚያንቋሽሸው፣ ያቺ ‘የገዥነት’ ነገር ስላለች ነው፡፡ ባል ሚስቱን… “በጊዜ ቤት ገብተሽ ካላገኘሁሽ አንቺን አያድርገኝ!” እያለ የሚያቅራራው፣ ያቺ ‘የገዥነት’ ነገር ስላለች ነው፡፡

ስሙኝማ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እነኚህ ስልጣንና ገንዘብ የሚሏቸው ነገሮች ይዘውት የሚመጡት የሆነ ወረርሽኝ አይነት ነገር አለ እንዴ! ልክ ነዋ…ሰዉ ገንዘብ ሲያገኝና ስልጣን ላይ ሲወጣ መጀመሪያ የሚታየው የሰዉን እንትናዬዎች መንጠቅ ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… የምር እኮ…ነገርየው ብሶበታል ነው የሚባለው። ልጄን ትምህርት ቤት ምን ያደርጉብኝ ይሆን! የሚባለው አልበቃ ብሎ፣ ምስኪን አባወራ…

“ሚስቴን ደግሞ ያ እብሪተኛ አለቃዋ፣ ምን ያደርጋት ይሆን!” ብሎ እንቅልፍ ማጣት አለበት እንዴ!
ቆይማ…እሱ ነገር ለአንዳንዱ “በቀን ሦስት ጊዜ ከምግብ በኋላ…” እየተባለ ይታዘዝ ጀመር እንዴ! እንደዛ ካልሆነ ለሁላችንም በፈረቃ የአንድ ወር ስልጣን ይሰጠንና “እስቲ እኛ እንዴት እንድምንንገበገብ ግቡና እዩት” እንባል፡፡ ከዛ ሁላችንም ስለምንነካካ ማን፣ ማን ላይ ይጠቁማል! ሁላችንም ‘ማኖ’ ነክተናላ! ‘ማኖ’ ነኪው ሲበዛ አቧራውም አይነሳም፡፡
እግረ መንገድ..ይቺን ስሙኝማ…እሱ፣ ለእሷ የሆነ የፍቅር ታሪክ እያነበበላት ነው፡፡ እሷዬዋ የሆነ ‘እነሆ በረከት’ ነገር ፈልጋ፣ ፊት ለፊት መጠየቅ ግራ ገብቷት፣ ዙሪያውን ትሽከረከር ነበር፡፡

እሷ፡— መጀመሪያው ገጽ ላይ ምን ይላል?
እሱ፡— የምትወዳት ሴት ስታገኝ በእጅህ እጇን ያዝ ይላል፡፡
እሷ፡— ከዛስ ምን ሆነ?
እሱ፡— ከዛ እጇን ትጨምቀዋለህ፡፡
እሷ፡— ከዛስ?
እሱ፡— ከዛ እጅህን በወገቧ ዙሪያ ታደርጋለህ።
እሷ፡— ቀጥል! ቀጥል!
እሱ፡— ፈጠንሽብኝ፡፡ ከዛ ለእግር ሽርሽር ይዘሀት ትወጣለህ፡፡
እሷ፡— እሺ! እሺ! ከዚያስ ምን ይላል?
እሱ፡— ውይ!…
እሷ፡— ምነው፣ ምን ሆንክ!
እሱ፡— የሚቀጥለው ገጽ ተቀዷል፡፡
እንዲህም ወሽመጥ ብጥስ የሚያድርግ ነገር አለ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ የሰርግ ሰሞንም አይደል… ሰዋችን እየተጋባ ነው፡፡ አኔ የምለው…“የአብረሀምና የሳራ ጋብቻ ይሁንላችሁ፣” የሚባለው ነገር ቀረ እንዴ! እና…የፔንሲዮን ማረፊያ ሲያስሱ ኖረው፣ የራሳቸው፣ “ሰዓት አልቋል፣ ውጡ…” የማይባልበት አልጋ ላይ ሲወጡ፣ ምን ሰይጣን ነው የሚገባባቸው! “አቶ እከሌና ወይዘሮ እከሊት 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን አከበሩ…” ሲባል ስንሰማ ለዚህ ዘመን በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡

እንግዲህ ስንት ውጣ ውረድ አልፈው፣ የገጠሟቸውን መሰናክሎች ሁሉ ተቋቁመው፣ ትንሹም ትልቁም ጥምረታቸውን እንዳይረብሸው ጥርሳቸውን ነክሰው፣ የወርቅ ኢዮቤልዩ ላይ መድረስ ማለት ቀላል ነገር አይደለም፡፡
የምር ግን…ያውም በዛ ዘመን እኮ እንዲህ “ከቀበሌ የላጤነት መረጃ አምጣ…” በማይባልበት፣ “እዚህም፣ እዚህም፣ እዚህም ላይ ፈርሙ…” በማይባልበት ዘመን… የተገባ ቃል፤ከተጻፈ ወረቀት በላይ ክብርና እምነት ይሰጠው በነበረ ዘመን የሆነ ነው፡፡ ያውም ሁለቱ ሳይተዋወቁ ወላጆቻቸው “ልጅህን ለልጄ” ተባብለው፣ ገና በህጻንነታቸው ማንን እንደሚያገቡ የተወሰነላቸው ናቸው፡፡ እንግዲሀ ለመፍረስ ቀላል ሊሆን የሚገባው ትዳር የዚህ አይነቱ ነበር፡፡

ግን ሀምሳና ከዛ በላይ ዓመታት በትዳር ቆይተው፣ በልጆችና በልጅ ልጆች ይከበባሉ፡፡ ዘንድሮ አይደለም ሀምሳ ዓመት፣ ሀምሳኛው ቀን ሳይደርስ ነው ነገር የሚበላሸው፡፡ እናም ቀደም ባለው ጊዜ አርባ፣ ሀምሳ ዓመት ሞላው እየተባለ የጋብቻ ዓመት ይቆጠር ነበር…ዘንድሮ ገና “ይዟት፣ ይዟት በረረ” ከተባለ መንፈቅ ሳይሞላው…አለ አይደል… “አሥራ አምስት”፣ “አሥራ ስድስት” እየተባለ ንብረት ቆጠራ ነው የተያዘው፡፡

“ትዳራችሁን ከዲያብሎስ ዓይን ይሰውርላችሁ…” የሚል ምርቃት ያስፈልገናል። ለነገሩማ… አለ አይደል… መራቂዎቹ እነማን እንደሚሆኑ እንጃ እንጂ በብዙ ነገሮች መንፈስ የሚያነቃቁ ምርቃቶች ያስፈልጉናል፡፡

“ምሳሀን ከግማሽ እንጎቻ ወደ ሙሉ እንጀራ ያሸጋግርልህ!”
“የሚበነው ሹሮ ወጥህ ላይ ስጋ ጣል፣ ጣል ያድርግልህ!”
“ቁርስህን አስቦ ከማርፈድ ዳቦ በሻይ ወደ መብላት ያሳድግልህ!”
የምር ምርቃት ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡ ቢሆንም፣ ባይሆንም ቃላቱን ‘ሪሳይክል’ እያደረግን መጽናናት እንችላለን፡፡
“እድሜ ለፎርጀሪ ምን ችግር አለው!” ሲለን ነበር አንድ ወዳጃችን…ለካስ ‘ፎርጅድ ባል’ የሚባል ነገር አለ፡፡ ባልም ከቻይና ይመጣ ጀመረ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ስለ ቻይና ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…አንድ የምዕራባውያን ቀልደኛ እንዲህ ብሎ ቀልዷል። “የቻይና ግምብ ከዓለም አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነው ከአራት ሳምንታት በላይ ሳይበላሽ የቆየ ብቸኛው የቻይና ምርት ስለሆነ ነው”
እናላችሁ ‘ፎርጅድ ባል’ እሷዬዋን የሚያገባው የእሷ ፍቅር፣ የደም ዝውውሩን አዛብቶት ሳይሆን የቤተሰቦቿ ሀብት፣ ደሙን ራሱ ላይ አውጥቶብት ነው፡፡ ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ዋናው ሥራው፤ የተቻለውን ያህል ሀብት ከቤተሰቦቿ ወደ ራሱ ማዞር ነው አሉ፡፡ እናማ… የልቡን ካደረሰ በኋላ እሷ ምን ታደርግለታለች!

ይቺን ስሙኝማ…አባት ልጁን ስለ ዓለም አፈጣጠር እየነገረው ነው፡፡
አባት፡— መጀመሪያ ዓለም ሲፈጠር አዳም ተወለደ፡፡
ልጅ፡— ጠዋት ነው የተወለደው?
አባት፡— አይደለም፤ ማምሻውን ነው የተወለደው፡፡ ከዛ ተኝቶ እንቅልፍ ሲወስደው፣ ከጎኑ አጥንት ተወሰደና ሔዋን ተፈጠረች፡፡
ልጅ፡— አዳም የጎን አጥንቱን አልፈለገውም ነበር?
አባት፡— ትርፍ አጥንት ስለነበረው ነው፡፡
(ይሄኔ ልጁ ማልቀስ ይጀምራል)
አባት፡— ደግሞ ምን ሆንክ?
ልጅ፡— አባዬ ጎኔን አመመኝ፡፡ ሚስት ላገኝ ነው መሰለኝ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

አዲስ አድማስ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram