fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ሙዚቃችንን ያሳደገውና ሙዚቀኞቻችን ያሳነሰው ቴዲ አፍሮ….

ሙዚቃችንን ያሳደገውና ሙዚቀኞቻችን ያሳነሰው ቴዲ አፍሮ….
(አሳዬ ደርቤ )

ቴዲ አፍሮ የህዝብን ልብ መግዛት የቻለ ታላቅ አርቲስት ነው፡፡ ይሄ ታላቅነቱ ደግሞ ጉሮሮ-ወለድ ሳይሆን በብዙ ጸጋዎች የመጣ ነው፡፡

ቴዲ ለዘፈኖቹ ግጥም ሲገጥም ሃሳቡን የሚወስደው ከህዝብ ልብ ውስጥ ነው፡፡ የሚመራውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በህዝብ ጭንቅላት ነው፡፡ ስለዚህም ከህዝብ የወሰዳቸውን ሃሳቦች በቃላትና በዜማ ቀምሮ ሲዘፍናቸው የሚመቱት የህዝብ ልብ እንጂ የከበደ ሚካኤልን ቤት አይደለም፡፡

ሲቀጥል ደግሞ ቴዲ ክብሩንና ህዝቡን በጥቅምም ሆነ በገንዘብ የማይለዉጥና ላመነበት ነገር የሚሞት ከባድ አርቲስት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› የሚል ዘፈን ባወጣ ማግስት 17 መርፌ ሳይሆን፤ 17 መድፍ እንደሚደገንበት ያውቅ ነበር፡፡

‹‹ዳህላክ ላይ ልስራ ቤቴን›› ብሎ ሲያቀነቅን….. ከቤቱ በፊት መቃብሩን እየቆፈረ መሆኑን አሳምሮ ይገነዘብ ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ልጁ ከመክሊት በተጨማሪ ድፍረት የተሰጠው ነውና ስሜቱን ለአድናቂዎቹ አካፍሎ የሚመጣውን ለመቀበል አይፈራም፡፡ ስለዚህም ቴዲ ያገኘው አድናቆት የሚያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም፡፡

ችግሩ ግን እኛ አድናቂዎቹ የእሱን ያህል ለማመዛዘን አልታደልንም፡፡ እሱ የሚያደንቃቸውንና እንደ ሮል-ሞደል የሚያየቸውን አርቲስቶች ሁሉ ክደን ዘርፉን ሁሉ ሙጥጥ አድርገን ለእሱ አስረክበነዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ ለሌሎች አርቲስቶች ብቻ ሳይሆን ለእርሱም ምቾት የማይሰጥ ቢሆንም እኛ ግን እያባስነው እንጂ እየቀነስነው አልመጣንም፡፡ የእኛ ጭፍን አድናቆት የእሱን ታዳሚ የመሆን መብትና የሌሎችን ሙዚቀኞች ሞራል የሚያንኮታኩት ቢሆንም ይሄንን ነገር የሚያስበው አልተገኘም፡፡

ለምሳሌ ያህል ባንድ ወቅት ላፎንቴኖች ህብረት የፈጠሩበትን በዓላቸውን ሲያከብሩ መድረክ መሪው ‹‹ቴዲ አፍሮና ጋሼ አበራ ሞላ በቦታው መገኘታቸውን በመግለጽ በቅድሚያ ጋሼ አበራን ወደ መድረኩ ጋበዘ፡፡

ታዳሚው ግን አልሰማውም፡፡ መድረክ ላይ የቆመውን አርቲስት ከምንም ሳይቆጥር ‹‹ቴዲ! ቴዲ! ቴዲ!‹‹ እያሉ መጮህ ጀመሩ፡፡

በወቅቱ ይሄንን ሁኔታ በቪድዮ ስመለከት እኔ በሃዘን ውስጥ ተውጬ ሳይ የነበረው የቴዲ አፍሮን መምጣት ሳይሆን የጋሸ አበራን ፊት ነበር፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ ሚሊኒዮም አዳራሽ ውስጥ የሃገራችን ታዋቂ አርቲስቶች ኮንሰርት አዘጋጅተው በርካታ ታዳሚ ተገኝቶ ነበር፡፡ እናም በዝግጅቱ መሃከል ቴድ አፍሮ ታዳሚ ሆኖ መገኘቱን የተገነዘበው ህዝብ፤ ከረዥም ጊዜ በኋላ መድረክ ላይ ተሰይሞ ሲዘፍን የነበረውን አንጋፋውን አርቲስት ‹‹ኤፍሬም ታምሩን›› መከታተሉን ችሎ የተለመደ ጩኸቱን መልቀቅ ጀመረ፡፡
ቴዲ! ቴዲ! ቴዲ!

በታዳሚው ጩኸት መሃከል ኤፍሬም ስሜቱን ተቆጣጥሮ ለመዝፈን ሞከረ፡፡ በመጨረሻ ግን ከአቅሙ በላይ ሆነበትና ‹‹አድናቆትን አገኝበታለሁ‹‹ ባለው መድረክ ላይ ንቄትን ሸምቶ በብስጭት ወረደ፡፡
.
የኢትዮጵያና የኤርትራን ስምምነት አስመልክቶ በተዘጋጀው ድግስ ላይም የሆነውም ይሄው ነበረ፡፡ መድረክ መሪው በዝግጁቱ ላይ የሚዘፍኑ አርቲስቶችን ሲዘረዝር የቴዲ አፍሮን ስም ያልጠቀሰ ቢሆንም ታዳሚው ግን ሃቁን መቀበል አልፈለገም፡፡

እናም መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ እድለኛ ዘፋኞች በጊታርና በሳክስ ሳይሆን ‹‹ቴዎድሮስ›› በሚል ድምጽ ታጅበው መዝፈን ቻሉ፡፡

የቴዲ መኖር ከታወቀ በኋላ ግን ይህችም እድል መክና አረፈች፡፡ ለመዝፈን የተዘጋጁትን አርቲስቶች ችላ ብለው ያልተዘጋጀውን ቴዲን እንዲዘፍን የሚወሰውሱ ድምጾች አዳራሹን ይንጡት ያዙ፡፡

ዝግጅቱ ላይ የተገኘው ህዝብ የሁለቱ አገሮች ስምምነት ምክንያት በማድረግ ሳይሆን በቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለማሸርገድ የመጣ ይመስል የተሰበሰበበትን አላማ ዘነጋ፡፡

ከሃያ ደቂቃ በጩኸት የተሞላ ጥበቃ በኋላ ቴዲ-አፍሮ ወደ መድረክ ወጥቶ የመሰለውንና የቻለውን ያህል በመዝፈንና ንግግር በማድረግ ህዝቡን ለማስደሰት ሞከረ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ታዳሚው መርካታ አልቻለም፡፡ እሱ ከመድረኩ ሲወርድ ህዝቡም አ,ዳራሹን ለቅቆ መውጣት ጀመረ፡፡

መድረክ መሪው ዝግጅቱ አለመጠናቀቁን በመግለጽ ታደለ ገመቹን ወደ መድረክ ጋበዘ፡፡ ችግሩ ግን መድረክ መሪውንም ሆነ ታደለ ገመቹን የሚሰማ ሰው አልተገኘም፡፡

ምን ይሄ ብቻ!

‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን አልበሙን ባልዘፈነው አርቲስት የተበሳጨው አደናቂ የኢትዮጵያን አንድነት ለመመለስ የሚጥረውን መሪውን በተቀመጠበት ችላ ብሎ ወደ ቤቱ ይሄድ ጀመር፡፡ በስንት ጥረት ሁለቱን አገሮች ያስታረቀውና የቴዲን ዘፈን እውን ያደረገው ጠቅላይ ሚኒስቴር ከእነ መኖሩም ተረሳ፡፡

ሃሳቤን ሳጠቃልለው ቴዲ አፍሮ ለእኛ ለአድናቂዎቹ ሙዚቀኛችን ብቻ ሳይሆን መዝናናትን የነፈግነው እስረኛችንም ጭምር ነው፡፡
ስለዚህም መፍትሔ የሚመስለኝ እኛ ባለንበት ቦታ ቴዲ አፍሮ ባይገኝ ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ቀብርም ላይ ቢሆን ካገኘነው እንደ መሸታ-ቤት አዝማሪ ‹‹ተነስና ዝፈንልን›› ማለታችን ስለማይቀር አርቲስቱ የመዝፈን እቅድ ከሌለው በስተቀር እኛ በታደምንበት ፕሮግራም ላይ ባይገኝ መልካም ይመስለኛል፡፡ (የታምራት ደስታ ስርዓተ ቀብር ላይም ቴዲን ያጋጠመው መንጋ ለዚህ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡)

ሲቀጥል ደግሞ አርቲስቶቻችን ለሞራላቸው የሚያስቡ ከሆነ…. ኮንሰርት ላይ እንዲዘፍኑ ሲጋበዙ… ከክፍያው በተጨማሪ ቴዲ አፍሮ ታዳሚ ሆኖ መገኘትና አለመገኘቱን ቢያጣሩ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እሱ ባለበት ቦታ የሚገኝ አርቲስት ንቄትን እንጂ አድናቆትን ባያስበው መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ቴዲ አፍሮ ሙዚቃችንን ለማሳደግና ሙዚቀኞቻችን ለማሳነስ የተፈጠረ ድንቅ አርቲስት ነውና! DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram