fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ሙሉአለም አበበ ማን ነው?

ሙሉአለም አበበን አብዛኛው ሰው የሚያውቀው በትግል ስሙ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ሙሉአለም የሚለው መጠሪያው የህዝቡ መልካም አስተዳደር እጦት ሲያንገበግበው ለትግል ወደ ጫካ ሲገባ ያገኘው የበረሃ ስሙ ነው፡፡
ወላጆቹ አዳነ ስብሃት ሰንደቄ የሚል ስም ነው ያወጡለት፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በቀድሞው ጸዳ ወረዳ አምቦ በር ቀበሌ ልዩ ስሙ ወዛባ በሚባል ቦታ ነው በ1952 ዓ/ም ይህችን አለም የተቀላቀላት፡፡
ሙሉአለም አበበ የእድል ጉዳይ ሆኖ ህይወቱ በአካባቢያዊ የአስተዳደር ችግር የተሞላ በመሆኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያደገው፡፡

ሙሉአለም የኪነጥበብ ክህሎትን ገና ከልጅነቱ የተላበሰ በመሆኑ በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ያንጎራጉር እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡
የሙዚቃ ተሰጥኦውን ያዳበረው እና ለጓደኞቹ የሚያሳየው ባብዛኛው በትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ተሰጥኦውን የተረዱት መምህራኖቹም የኪነጥበብ ተሰጥኦው ትልቅ ቦታ እንደሚያደርሰው በመግለጽ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ይመክሩትም ነበር፡፡
በሙዚቃ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ብሔራዊ መዝሙሮችን፣ ሙዚቃዎችን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚለቀቁ ሙዚቃዎችን በተለየ አተያይ ገልብጦ በመዝፈን የነበረውን ተሰጥኦ ያሳየም ሰው ነው፡፡

ሙሉአለም አበበ እንዲህ እንዲህ እያለ ህይወቱን እየገፋ ቢቆይም በወቅቱ የነበረው የወታደራዊው ደርግ ስርዓት እየከፋ እና ወጣቶችን ማሳደድና መግደል በመጀመሩ ስቃዩ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም መታገል እንዳለበት በመወሰን ትምህርቴ፤ቤተሰቤ ሳይል ሁሉን ትቶ ጫካ ገባ፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር ወላጆቹ ያወጡለት አዳነ ስብሃት ሰንደቄ ቀርቶ ሙሉአለም አበበ የሚል ስም የወጣለት፡፡
ሙሉአለም አበበ በ1970 ዓ/ም ትግሉን ሲቀላቀል በነበረው ተሰጥኦ እና በታጠቀው ነፍጥ ጨቋኙን ስርአት በመገርሰስ እና በምትኩ እኩልነት የሰፈነባት፤ሁሉም እንደፍላጎቱ የሚኖርባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት ተነሳሳ፡፡
በውስጡ የነበረው የኪነጥበብ ተሰጥኦ ታግሎ ለማታገል እንደ ሁለተኛ መሳሪያነት እንደሚያገለግል በመረዳቱ የኪነጥበብ ተሰጥኦውን ሳይሰስት ለታጋዮች በማድረስ የትግሉ ምእራፍ በድል እንዲታጀብ ያደረገ ጀግና ነበረ፡፡
ሙሉአለም አበበ የትግል ድርጅቱን ኢህዴንን ከተቀላቀለ በኋላ በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች ላይ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

ይሰራቸው የነበሩ የግጥም ስራዎች፤የሙዚቃ ውዝዋዜዎች እና የድምጽ ቅላጼዎች አብዛኛውን ታጋይ ያስደስቱ ስለነበር ለትግሉ ብርታት ሆኗል፡፡
በዚህ ክህሎቱም ሁሉም ቦታ ላይ እንዲገኝ እና ታጋዮችን እንዲያዝናና ይጋበዝም ነበር፡፡
ታጋይ ሙሉአለም አበበ በታጋዮች መካከል ፍቅር እንዲጠነክር እና አለመግባባቶች እንዳይኖሩ የሚያደርጉ ስራዎችንም ይሰራ ነበር፡፡

በተለይም ይሰራቸው የነበሩት ግጥሞች ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በትግሉ ውስጥ የተሰለፉ ታጋዮች ለችግሮቹ መፍትሔ በማምጣት፤ለህይወታቸው ሳይሰስቱ እንዲታገሉ ብርታት እንደነበሩ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡
ታጋይ ሙሉአለም ከድል በኋላ ከኪነጥበብ ችሎታው እና ከታጋይነቱ ባሻገር ህዝብን የመምራት ብቃቱን በማሳየቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ይህን ጀግና ለማስታወስ እና ባለውለታነቱን በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ተቀርጾ እንዲቀር ለማድረግ በክልሉ ርዕሰ መዲና ባህር ዳር የሙሉአለም የባህል ማዕከልን አስገንብቷል፡፡
ክልሉ በሙሉአለም መታሰቢያ ማዕከል አማካኝነት የክልሉ ባህል ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚል በአዋጅ ቁጥር 24/1996 የባህል ማዕከል በማቋቋም ስራዎች እንዲሰሩ እያደረገ ይገኛል፡፡
በአዋጅ የተቋቋመው የሙሉአለም የባህል ማዕከል ዋና አላማ የክልሉ ባህላዊ ትውፊት ተጠብቆ እንዲቆይ በኪነጥበብ ትውልዱን ማስተማር በመሆኑ የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችንና ውዝዋዜዎችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

የሙሉአለም የባህል ማዕከል የባህል ፕሮግራሞች ዝግጅት ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙላት ዋለ ለድረገጻችን በሰጡት አስተያየት፤የባህል ማዕከሉ የሙሉአለም አበበን የኪነጥበብ አበርክቶ ሳይለቅ የክልሉን ባህል በጠበቀ መንገድ ትውፊታዊ ቲያትር እያዘጋጀ ለክልሉ ህዝብ በማሳየት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ አመትም የራያ ቆቦን ባህላዊ ትውፊትን በማጥናት እና ወደ ቲያትር በመቀየር ለማስተማር በመቻሉ ተወዳጅነትን ማግኘት ችሏል ብለውናል፡፡

አቶ ሙላት በመቀጠልም ማዕከሉ የሙሉ ጊዜ ቲያትር ሰርቶ ለእይታ የማብቃት ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ በዚህ አመት ‹ የመጨረሻው መንገደኛ › የተሰኘ ቲያትር ለህዝብ አድርሷል ነው ያሉት፡፡
ማዕከሉ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ምጥን ተውኔት አንዱ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሙላት በዚህ አመት ከሀገር ውጭ ወደሱዳን ገዳሪፍ በመጓዝ ስራዎችን አቅርቧል ብለውናል፡፡

የሙለአለም የባህል ማዕከል የታጋይ ሙሉአለም አበበን የትግል እና የኪነጥበብ ልምድ በመከተል ከሰላም ጋር የተያያዘ ቲያትር ሰርቶ ለዕይታ ያበቃ ሲሆን በክልሉ ባሉ 5 ዩኒቨርሲቲዎች እና ከክልሉ ውጭ ባሉ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች በማሳየት እውቅና ማግነቱን ነው አቶ ሙላት የነገሩን፡፡

ሙሉአለም የባህል ማዕከል – ባሕር ዳር

የቻይናው ሲልክ ሮድ ኢንተርናሽናል በሚሠራቸው ስራዎች እውቅና በመስጠት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 ባህል ማዕከሉ አባል እንዲሆን የፈቀደለት ሲሆን በዚህ አመት ደግሞ የእውቅና ሰርተፊኬት ሰጥቶታል፡፡
በዚህ ረገድ የሙሉአለም ባህል ማዕከል በሀገሪቱ ይህን እውቅና ያገኘ የመጀመሪያው ባህል ማዕከል መሆንም ችሏል፡፡
ታጋይ ሙሉአለም አበበ ምንም እንኳን ባልታወቀ ድንገተኛ አደጋ ሚያዝያ 1985 ዓም ህይወቱ ቢያልፍም ተሞክሮዎቹ ግን አሁንም ድረስ ለመላው ህዝብ ስንቅ መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ – አብመድ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram