fbpx

መንግስት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ያሳለፈው ውሳኔ የተለያዩ ምላሾች እያስተናገደ ነው

የዛሬ አንድ ወር ወይም ሚያዝያ 28 ቀን ሲከበር በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ይገባኛል ጦርነት መጀመርን 20ኛ አመት አስመልክተው በርካታ ዘገባዎችን አስነበቡ፡፡ ብዙዎች የሁለቱ አንድ የነበሩና ጎረቤታሞች የሆኑ ሀገራት ግጭት ለሁለት አስርታት ምስራቅ አፍሪካን ጭምር ያመሰ ጉዳይ መሆኑን አወሱ፡፡ ይህ ግጭት በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቢደመደምም ሀገራቱ እንደተፋጠጡ የዘለቁበትን ምክንያት በሰፊው አጠያየቁ ከዚህ በመነሳትም ሁለቱ ሀገሮች መቼ ይሆን ሙሉ እርቅ የሚያሰፍኑት በማለት ጠየቁ፡፡ የዛሬ አንድ ወር አሜሪካ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ጥረት መጀመሯ የሚራገብበት ወቅት በመሆኑ ይህ የተስፋ ጭላንጭል ይሰምር ይሆን ወይ በማለት በርካታ የመገናኛ ብዙሀን ሲጠይቁ ነበር የከረሙት፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ባበቃ በ 20ኛ አመቱ የሰላም ጭላንጭል መፈንጠቁን ታዋቂው ተንታኝ አወል አሎ በአልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ዘገባ በሰፊው ካስነበቡት አንዱ ነበሩ፡፡ ጸሀፊው በዚህ ትንተናቸው ላይ ካሰፈሩት ተከታዩን ነጥብ እናገኛለን፡፡

ለሁለት አመታት የተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለምንም ይሆናል ተብሎ ብዙም በማይገመት ባድሜ በተባለ መሬት ይገባኛል የተጀመረ ነበር፡፡ ከአፍሪካ እጅግ የሰለጠነ ጦር ያሰለፈውን የቀድሞ ስርአት በጋራ ተዋግተው ያሸነፉት መለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ፍጹማዊነት ተቀየሩ፡፡ የኤርትራና ኢትዮጵያ መለያየት በሂደት ቅርጹን ሲለውጥና የግንኙነታቸው መረብ ሲበጠስም ጦርነቱ ተቀሰቀሰ የሚል ትንተና ይሰጣል፡፡ የዚህ ጦርነት መቀስቀስ ውጤት ግን ልክ እንደ አንደኛው የአለም ጦርነት ጠንካራ የምሽግ ውጊያን አስከትሎ 100 ሺህ ሰው አለቀ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አፈናቀለ እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ገመድ በጠሰው በማለት ጸሀፊው ይዘረዝራሉ፡፡

ሁለቱ ሀገሮች በዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት የከፈሉት ዋጋ ብዙ ነበር፡፡ እጅግ ውድ የሆነውን የዜጎቻቸውን ህይወት ከመገበር ባለፈ አንጡራ ሀብታቸውን አራቁተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጊዜው የጦር ሰራዊት ቁጥሯን በአንድ ጊዜ ከ 60 ሺህ ወደ 350 ሺህ አሳደገች፡፡ የሀገሪቱ የጦር በጀት በአውሮፓዊያኑ 1997/98 ላይ ከነበረበት 95 ሚሊዮን ዶላር በ 1999/2000 ወደ 777 ሚሊዮን ዶላር አሻቀበ፡፡ ሀገሪቱ በአጠቃላይ ለጦርነቱ እስከ 3 ቢሊዮን ዶላርም ከስክሳለች፡፡ በኤርትራ በኩልም በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ስም ከህዝቧ 10 በመቶውን ማለትን 300 ሺህ ዜጎችን ለጦር አሰለፈች በማለት ተንታኙ ሀሳባቸውን ይቀጥላሉ፡፡

አወል አሎ ይህን ዘገባ ካስነበቡ ከአንድ ወር በኋላ ትናንት የኢትዮጵያ መንግስት የድንበር ውሳኔውን እቀበላለሁ የሚል መግለጫ ይፋ አደረገ፡፡ ይህ በተሰማ ወቅትም እኚህ ጸሀፊ በትዊተር ገጻቸው ላይ “ኢትዮጵያ የድንበር ውሳኔውን ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል መስማማቷ የግጭቱ መነሻ ከሆኑ ድንበሮች አንዱ ባድሜን ለኤርትራ ያስገኝላታል፡፡ ይህ ውሳኔ ለሁለቱ ሀገራትም ሆነ ለአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ብልህ እርምጃ ወሰደ፤ አሁን ኳሱ ሙሉ ለሙሉ በኢሳያስ አፈወርቂ ሜዳ ነው” በማለት ስለ አዲሱ እርምጃ የጻፉት፡፡

ይህ ጦርነት ከተደረገ በኋላ በነበሩት 20 አመታት ሁለቱ ሀገራት በጂኦ-ፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ኖረዋል የሚሉት አወል አሎ የጦርነቱ መንስኤ፣ የአልጀርሱ ስምምነት፣ ጦርነቱ ያስከተለው ውጤትና አሁን ፈነጠቀ ያሉትን የሰላም ብልጭታ በዝርዝር ይፈትሹታል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ በለንደን ዩኒቨርሲቲ የኮመንዌልዝ ስተዲስ የሚሰሩት ታዋቂው የጂኦ-ፖለቲካዊ ተንታኝ ማርቲን ፕላውት ኢትዮጵያና ኤርትራ ከደም አፋሳሹ ጦርነት 20 አመት በኋላ እርቅ ለማውረድ ይችሉ ይሆንን ሲሉ በጥያቄ ሰፊ ትንታኔን አስነብበው ነበር፡፡ ተንታኙ በዚህ ሀተታቸው ደግሞ የሚከተለውን ፍሬ ነገር አስቀምጠው እናገኛለን፡፡

በአፍሪካ ግጭት የተለመደ ቢሆንም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረገውና ልክ በዛሬዋ ቀን ከ 20 አመት በፊት የፈነዳው ጦርነት ግን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በአህጉሪቱ ያልታየ አይነት ነበር፡፡ ይህ ጦርነት አፍሪካ እንደለመደችው ገጀራና መሳሪያ በታጠቁ አማጺያንና ወታደሮች መካከል የተካሄደ መገዳደል አይነት አልነበረም፡፡ ይህ ጦርነት እስከ ጦር አውሮፕላን ድረስ ሙሉ የጦር ትጥቅና ሀይልን ያሰለፈ መደበኛ ውጊያ ነበር፡፡ የሞተውና የቆሰለውን ቁጥር ማንም እስከአሁን ባያውቅም 100 ሺህ ሰው ከሁለቱም ወገን መገደሉ ይገመታል፡፡

የዚህ ጦርነት ውጤት ደግሞ ባለፉት 20 አመታት መላውን ምስራቅ አፍሪካን ልክ እንደ ጥቁር ዳመና የጋረደ ነበር፡፡ ሰኔ 18/2000 ዓ/ም እንደፈረንጆቹ የተፈረመው የአልጀርሱ ስምምነት ጦርነቱን የማስቆም አላማ ነበረው፡፡ ሁለቱ ወገኖች የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ዳኝነት እንዲያከብሩ፣ የተመድ ጦር በድንበሮቻቸው እንዲሰፍር፣ ምርኮኞች እንዲለዋወጡና ካሳ እንዲከፍሉ ቢደረግም ይሁን እንጂ ላለፉት 20 አመታት ከነውጥረታቸው ነው ያሳለፉት፡፡ ወታደሮቻቸው አሁንም እንደተፋጠጡ ሲሆኑ በድንበሮቻቸው አካባቢ ሁሉም እንቅስቃሴ ቆሞና ግንኙነታቸው ተበጥሶ ነው የቀሩት በማለት ጸሀፊው ማርቲን ፕላውት የያኔውን ግጭት እየተፈጠሩ ካሉ የሰላም እድሎች ጋር አያይዘው በሰፊው አስተንትነውታል፡፡

ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ይህ ሁሉ ጉዳይ በተነሳ በአንድ ወሩ ግን ያልተጠበቀ ነገር ትላንት ተከሰተ፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነት እንደሚቀበለው አስታወቀ፡፡ ብዙዎች የኢትዮጵያ መንግስት ያን ሁሉ ዋጋ ካስከፈለ ጦርነት በኋላ ድንበሩን ለኤርትራ አሳልፎ ሰጠ በሚል ጉዳዩን እየተቀባበሉት ይገኛል፡፡ አንዳንዶች ከበጣም መጥፎ መጥፎ በሚል ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአለም አቀፉን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲቀበሉ ነበር የኢትዮጵያ መንግስት ድንበር የሰጠው በማለት የቀደሙ አመራሮችን ኮንነው የአሁኑን መንግስት ተከላከሉ፡፡

 

በዚሁ የኢትዮጵያ መንግስት ያልተጠበቀ ውሳኔ ላይ ለቪኦኤ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ደግሞ አጋጣሚው ለሁለቱ ሀገሮች ዘላቂ ሰላም ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት የኤርትራ አማካሪ በመሆን የሚታወቁትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ አተገባበር የታዘቡት የዬል ዩኒቨርሲቲ የህግ ፕሮፌሰሯ ሊ በርልማየር የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ መነሻው ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደሚከብድ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ ከልብ የሆነና የሚተገበር ከሆነ ትልቅ እርምጃ መሆኑ አይቀርም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ የድንበር ውሳኔውን አክብራ ጦሯን ካካባቢው ካስወጣች ኤርትራን ተመሳሳይ እርምጃ እንዳትወስድ የሚያግዳት አንዳችም ምክንያት አይኖርም በማለት ፕሮፌሰሯ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ በፈረንጆቹ 2013 ላይ የኤርትራው አምባሳደር ግርማ አስመሮም ኢትዮጵያ ነገ ጠዋት ጦሯን ካስወጣች ከሰአት በኋላ ወደጠረጴዛ ድርድር እንመጣለን ያሉበትን ንግግር የሚያስታውሰው ቪኦኤ ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት ውሳኔ ምናልባትም የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ የሚቀይር ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ ነው ዘገባውን የደመደመው፡፡

ሪክ ግላድስተን ትናንት የተሰማውን የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ ተከትሎ በ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባው ላይ ባሰፈረው ዘገባ ደግሞ በአትላንቲክ ካውንስል ጥናት ተቋም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ብሮንዋይን ብሩተን የሰጡትን ሀሳብ ይጠቅሳል፡፡ የኤርትራ አቋም ሁሌም ቢሆን የድንበር ውሳኔው ይከበር የሚል ሆኖ መቆየቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ ብሩተን ኤርትራዊያኑ ትክክለኛ መንገድ ላይ እንደነበሩ ያምናሉ ብለዋል፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ የሁለቱን ሀገሮች ችግር ለመፍታት መቆርጦ መነሳቱን ያሳያል፡፡ ውሳኔው ከኤርትራ በኩል ግጭቱን ለመፍታት ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ነው በማለት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የትናንቱ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ በዜጎች መካከል ዋና መነጋገሪያ ጉዳይ ጭምር ሆኗል፡፡ ይህን በሚመለከት ደግሞ ሸገር ታይምስ ተቃዋሚዎች፣ ተንታኞች እና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሉትን ሀሳብ በተከታታይ ይዛ ለመቅረብ የምትሞክር ይሆናል፡፡

ምንጭ፡- ሸገር ታይምስ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram