fbpx

መንግስቱ ኃ/ማርያም በግንቦት 13 ሲታወሱ

ታሪክን የኋሊት፣ ግንቦት 13፣2010

ኢትዮጵያን ለ17 አመታት እንደፈቀዱና እንደፈለጉ በኃይል ሲገዙና ሲነዱ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም፣ የተቃዋሚ የጦር ሀይል ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ፣ ሸሽተው ከሀገር የወጡት ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬው ቀን ነበር፡፡ እለቱ ማክሰኞ ነበር፡፡ በስድስት ሰዓቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ የዜና እወጃ፣ በሀገሪቱ ያለውን ደም ማፍሰስ ለማስቆም ሲባል ፕሬዚዳንት መንግስቱ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ ተነገረ፡፡ በማግስቱ ግን ኘሬዝዳንቱ ከሃገር የወጡት ለማንም ሳያሳውቁ ሸሸተው መሆኑን የመንግስት ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ ሌፍተናንት ጀነራል ተስፋዬ ገ/ኪዳንም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሰየሙት በዚያው ቀን ነበር፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ፣ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅ በአዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት እጁ ያደረገው ወታደራዊ ጁንታ (ደርግ) ሊቀመንበር ነበሩ፡፡

የኢሠፓ ዋና ፀሀፊ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በሚል በተደራረቡ ሹመቶች ራሳቸውን ሾመው ኖሩ፡፡ ይሁንና አስተዳደራቸው ገና ከጅምሩ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ግድያና ደም ማፍሰስ ዋና አማራጭ በማድረጉ ተቃዋሚው በረከተ፡፡ መንግስታቸውን በመቃወም ተቃዋሚ ሀይሎችም ጠመንጃ አንስተው ጥቃት ጀምረው ድል አገኙ፡፡ በሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት ዓ.ም አጋማሽ ላይ፣ ተቃዋሚው የኢህአዴግ ሰራዊትም ወደ አዲስ አበባ በአሸናፊነት ገሰገሰ፡፡ የጦር ጥቃት እንደተጠጋቸው ያዩት ኮሎኔል መንግስቱ፣ “እምንሞተው እምንኖረውም እዚሁ ሀገራችን ላይ ነው” የሚለውን ፉከራቸውን ሰርዘው “ግንባሬ እስከተበተነ ድረስ ትግሌን እቀጥላለሁ” ይሉ የነበሩትን መፈክር አጥፈው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ኬንያ ፈረጠጡ፡፡ የተሳፈሩበት አውሮፕላን እንዚዘጋጀላቸው ያደረጉት በብላቴና ወታደራዊ ማስልጠኛ ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ የነበሩትን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እጐበኛለሁ በሚል ሰበብ ነበር፡፡

ከብላቴና ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በሚል ሰበብ፣ አውሮፕላኗ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ፡፡ ረፋድ ላይ በረራቸውን ጀመሩ፡፡ ግን በአየር ላይ እንዳሉ አውሮፕላኑ ወደ ናይሮቢ እንዲበር አብራሪውን አስገደዱት፡፡ አብራሪው፣ ለኬንያ በረራ እንዳልተዘጋጀ የኬንያ ካርታ እንደሌለው እና መብረር እንደማይችል አሳወቀ፡፡ ኮሎኔሉ ግን “በግድ ትሄዳታለህ” ብለው አቅጣጫውን ለውጦ እንዲበር አስገደዱት፡፡ በዚህ ድርጊታቸውም የሀገር መሪ ሆነው፣ አውሮፕላን ለመጥለፍ፣ የመጀመሪያው መሪ ተብለዋል፡፡ ናይሮቢ አውሪፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛ ፀሀፊ ተቀበሏቸው በዛያው የስደተኝነት ኑሩዋቸውን ወደሚገፉበት፣ ወደ ሀራሬ ከአምስት አጀቢዎቻቸው ጋር አይሮኘላን ለውጠው ሾለኩ፡፡ በኋላ ላይ ኘሬዝዳንት ሙጋቤ እንዳረጋገጡት ኮሎኔል መንግሥቱ ከሃገር የሸሹት በተጠና እቅድ ነበር፡፡

ኮሎኔል መንግስቱ፣ በስልጣን ዘመናቸው ሀገሪቱን እርስ በርስ በሚያፋጅ ፖሊሲ፣ ለስልጣናቸው ቅድሚያ ሰጥተው፣ ሀገሪቱን የስቃይ እና የፍዳ መፈልፊያ አደረጓት፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ውርደትም ከተቷት የሚሏቸው ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የመሬት አዋጅን የመሳሰሉ ለማስፈፀም ጥረት አድርገዋል ይሏቸዋል፡፡ ሁሉም ግን በስልጣን ጥማት የታወሩ መሆናቸው እና በዚህም ከመጡባቸው ማንኛውንም ግፍ ለመፈፀም የማይተኙ አምባገነን መሆናቸውን ያረጋግጡባቸዋል፡፡ በዘመነ መንግስታቸው፣ እርስ በርስ በተደረገ ፍጀት እና ጦርነት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች አልቀዋል፡፡ ሥልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ የደርግ አባል ጓደኞቻቸውን ሳይቀር ሲቪልና የጦር አዛዦች ምሁራንና ገበሬዎችን ጨፍጭፈዋል፡፡ በሃገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ አገዳደል እንዲከናወን በማድረጋቸው ይታወቃሉ፡፡

በርሣቸው የአገዛዝ አመታት ገደል በመወርመር ፣ በበሬ በማስጎተት ፣ አስክሬን ጭንቅላት እያስቆረጡ በመስቀል ገበያ ላይ የአይሮኘላን ቦምብ በማስጣል ሕዝቡ ጭጭ ብሎ እንዲገዛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች በረሃብ ሲረግፉ ለሕዝብ እንዳይገለፅ በመካከላቸው ፅኑ እልቂት እንዲሆን ምክንያት ሆነዋል፡፡ የመናገርና የመደራጀት የመዘዋወር መብቶች እንኳን በውን በሕልም የማይታሰቡበት “ሀገር ማለት መንግስቱ እና ፓርቲው ብቻ ነው” ተብሎ እንዲታመን የሚያደርግ አሰራር የሚከተሉ መሆናቸው በተለያየ ጊዜ ተዘግቧል፡፡

መጨረሻቸው ግን፣ የፎከሩበትን ሁሉ ሳይፈፅሙ፣ ደጋፊዎቻቸው የሰጧቸውን “ቆራጡ” የሚል ስያሜ ተግባራዊ ሳያደርጉ፣ ሁሉንም ጣጥለው እግሬ አውጭኝ ብለው ጠፉ፡፡ የዘር ጭፍጨፋን ሲያይ የነበረው ልዩ ፍርድ ቤት በኮሎኔል መንግሥቱ ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸዋል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ አሁንም በስደት በሀራሬ እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡ ሌፍተናል ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን በ8 ቀናት የስልጣን ቆይታቸው፣ በአዲስ አበባ እልቂት እንዳይፈፀም፣ ሰራዊቱ ጠመንጃውን እንዲያስቀምጥ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ስራ ሊሰሩ አልበቁም፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ፣ በሸሹ በ8ተኛው ቀን፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ Sheger FM

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram