fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

መንግሥታችን ሆይ፤ ለደመወዝ ማስተካከያ ፍጠን!

መንግሥታችን ሆይ፤ ለደመወዝ ማስተካከያ ፍጠን!

መንግሥታችን ሆይ፤ ለደመወዝ ማስተካከያ ፍጠን! | በጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ

የሪፓርተር ጋዜጣ አንድ ዜና እንዲህ ይላል። ‘በሠራተኛ ፍልሰት ምክንያት መንግሥት የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መዘጋጀቱ ተሰማ።’

እህ!…መንግሥታችን ገና ዝግጅት ላይ ነው?! ይገርማል!!…አንድ የሰነበተ ጥናት ከመንግሥት ሠራተኛው 60 በመቶ ገደማ ወርሀዊ ደመወዙ ከ3 ሺህ ብር በታች ነው ይላል።

ይቀጥልናም የግሉ ዘርፍ አማካይ የደመወዝ ክፍያ ከመንግሥት ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ያትታል።

ጥናቱን አቆይተነው የመንግሥት ሠራተኛው በአስማት እየኖረ መሆኑን ጥቂት ማሳያዎችን እንጠቃቅስ። ዛሬ በመሀል የአዲስአበባ ከተማ ባለአንድ መኝታ ኮንደምኒየም ወርሀዊ የኪራይ ዋጋ ከ4 እስከ 5 ሺህ ብር ደርሷል። ባለሁለት መኝታ ከ 7 እስከ 9 ሺህ ብር እየተከራየ ነው። ልብ በል!.. በአንድ በወር የተጣራ 10 ሺህ ብር ደመወዝ ኪስህ ሊገባ የሚችለው ቢያንስ ከ13 ሺ 500 ብር በላይ ወርሀዊ ደመወዝ ሲኖርህ ነው።

እናም ባለ10 ሺው ትልቁ ደመወዝተኛ የመንግሥት ሠራተኛ የገቢውን ግማሽ አውጥቶ ባለአንድ ክፍል ኮንደምኒየም ለመከራየት አቅም የለውም። ሂሳብ የማይገባው ደፋር ሆኖ ተከራየ እንኳ ቢባል፤ የቀለብ፣ የልጆች ት/ ቤት፣ የትራንስፖርት ወዘተ ወጪዎች ሲደማመሩ ኑሮውን ሲኦል ማድረጋቸው የማይቀር ይሆናል።

አንዳንዶች ይህን መሰል ችግር ለመቋቋም ርካሽ ቤት ፍለጋ ከከተማ መራቅን እንደአንድ አማራጭ ሲወስዱት ይታያሉ። ይህም የራሱ ቀውስ አለው። ሠራተኞች በትራንስፖርት ችግር እንዲሰቃዩ ብቻም ሳይሆን በፍጥነት በሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው ምርታማነት ወይንም የዕለት ተዕለት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲጎአደል አንድ ምክንያት ይሆናል። ለቤተሰባቸው፣ ለልጆቻቸው የማይመች ነገር መፈጠር አእምሮአቸውን ሠላም ይነሳል።

በየመንግሥት ተቋማቱ የፋይናንስ ቀውስ ያለባቸው ሠራተኞች፣ አመራሮች እየበዙ መሄድ ሳይነጋገሩ፣ ሳይደራጁ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተባባሪ አካላት እንዲበራከቱ በር ይከፍታል።

በአንጻሩ የተማረውና በሙያው በቂ ልምድ ያለው ሐይል የተሻለ ጥቅም ፍለጋ በተንቀሳቀሰ ቁጥር የመንግሥት ሥራ አንቀሳቃሽ ያጣል። የአገልግሎት ጥራት ያሽቆለቁላል። በሌላ አነጋገር አገርና ሕዝብ የሚተዳደርባቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎች…ሳይቀር አቅም በሌላቸው ሰዎች የመዘጋጀታቸው ነገር የግድ ይሆናል። ይህ ደግሞ እንደአገር ኪሳራው የከፋ ይሆናል።

ዝቅተኛውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛም ምንም እንኳን ብድግ ብሎ ሥራ መቀየር ለግዜው ቢቸገርም በሥራው ደስተኛ አለመሆኑ ብቻ በመንግስት ተቋማት እንዲሰፍን የሚፈለገው የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎች መገዳደሩ አይቀርም።

እናም በአጭሩ መንግሥት ለሠራተኞቹ በቂ የደመወዝ ክፍያና ጥቅማጥቅም መስጠት ባለመቻሉ ክፉኛ ከስሯል። የሠራተኞችን ክፍያና ጥቅማ ጥቅምን በማሻሻል ብቻ በከፍተኛ ደረጃ ምርታማነትን፣ የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ማስፈን እንደሚቻል በቅጡ አለመረዳቱ እጅግ ከባድ ኪሳራና ቀውስ እያስከተለበት ይገኛል።

አዎ! መንግሥት እጅግ ዘግይቶም ቢሆን የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ማሰቡ የሚደገፍ ነው። አዎ! ቢያንስ ሰዎች መንግሥትን በማገልገላቸው ብቻ ሊቀጡ እንደማይገባ መረዳቱ የመጀመሪያው ጥሩ ነገር ነው። ሌላው ጥሩ ነገር የመንግሥት ሠራተኛው ብሶት፣ቁጣ ገንፍሎ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት መልስ ማግኘቱ ነው። እናም መንግሥት ሆይ ማህበራዊ ችግሩ ጎርፍ ሆኖ ሳይጠርግህ በፊት ፍጠን!… አዎ! ፍጠን!  DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram