fbpx

መልዕክተ ሓዳስ ኤርትራ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ አገላለጽ ‹‹ሞት አልባው›› የተባለው ጦርነት የተካሄደበት ዘመን አልፎ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ዳግም በታደሰ ማግስት ከታዩት ለውጦች አንዱ የስልክ ግንኙነት መጀመሩ የሚጠቀስ ነውና፤ የአዲስ ዘመን አቻ ወደሆነውና ሓዳስ ኤርትራ ወደ ሚሰኘው ከሰኞ በስተቀር ወደ ሚታተመው የኤርትራ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስልክ ደውለናል፡፡

ለዓመታት ያልተጫንናቸውን የመደበኛ ስልክ ቁልፎች በየተራ በመንካት ወደ ዝግጅት ክፍሉ ደውለን ‹‹ሄሎ›› ስንል ያገኘነው ዋና አዘጋጁን አቶ ኣስፍሃ ተኸለማርያምን ነበር፡፡ ተጠፋፍተው የከረሙ ወንድማማቾች ሲገናኙ የሚለዋወጡትን ሰላምታ በማስቀድም ወገን፣ አገር እንዴት ነው? ተባብለናል፡፡ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ተቋርጦ በነበረበት ሁለት አስርት ዓመታትም ቁርሾውን በተመለከተ የሚካሄዱ የቃላት ጦርነቶችን በማስተጋባት ረገድ በየአገራቱ የሚገኙት የመገናኛ ብዙሃን አሉታዊ ሚና መጫወታቸው ይነገራልና፤ ዛሬ በሁለቱ አገራት የሚገኝ አንድ ህዝብ ግንኙነቱ በቀና ጎዳና ይጓዝ ዘንድ የሓዳስ ኤርትራ ባልደረቦች መልእክት ምን ይሆን ? ስንልም ጠይቀናል፡፡

የሓዳስ ኤርትራ ዋና አዘጋጅ አቶ ኣስፍሃ እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት ከቃላት መረጣ ጀምሮ በሁለቱም ወገን የሚሰራጩት የመገናኛ ብዙሃን ይዘቶች አፍራሽነት ይታይባቸው ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ታሪክ ሆኗል፤ ነባሮቹም ሆኑ ወጣቶቹ ጋዜጠኞች ዳግም የታደሰውን ግንኙነት የሚያጎሉ ዘገባዎች እየሰሩ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደ ኤርትራ ለጉብኝት ከሄዱበት እለት ጀምሮ በአራት ቋንቋ በሚዘጋጁት ጋዜጦች ይንጸባረቃል፡፡ አገራቱ ያለፈውን ረስተው መጪውን ተሰፋ በማድረግ በንጹህ የወንድማማችነት መንፈስ ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ቃላቸውን በማደሳቸው መገናኛ ብዙሃኑም ይህን ማገዝ አለባቸው፡፡

‹‹ለሃያ ዓመታት በኩርፊያ የቆዩት ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰለጠነ መንገድ ችግሮቻቸውንና ልዩነታቸውን ለመፍታት የጀመሩት መንገድ አስደሳች ነው›› በማለት ሃሳባቸውን የሚገልጹት ዋና አዘጋጁ ፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተንጸባረቀው የህዝብ ስሜት ትብብሩ ዘላቂ እንዲሆን ጉልበት እንደሚሰጠው ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ሰለሞን በርሄ የኤርትራ ፕሬስ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው፡፡ ደርግን ለመጣል በተደረገው የትግል ወቅት ታንከኛ እንደነበሩ አስታውሰው ‹‹ከታንከኛ ወደ ጋዜጠኛ ተቀይሬአለሁ›› በማለት ጉዳዩን በማዋዛት ከጀመሩ በኋላ፤ ባለፉት ሃያ ዓመታ በሁለቱ አገራት መካከል የቃላት ጦርነት ይካሄድ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ቃላት መርዝ ሊሆኑ ይችላሉ›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ከእንግዲህ የሰላም እና የፍቅር ቃላት መዝራት ይጠበቃል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ ‹‹ሁለቱ ሀገራት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በስነ ልቦና እና በሃይማኖት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝብ በተለየ መልኩ በጣም የሚቀራረቡ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንድ ህዝብ ናቸው ማለት ይቻላል›› በማለት፤ የሁለቱ ሀገራት መገናኛ ብዙሃንም መልካም ጉርብትና እንዲዳብር እና ሁለቱ ህዝቦች እንዲቀራረቡ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በህዝቦች መካከል ያሉት የሚያቀራርቡ እሴቶች የሀገራቱን ሰላም ለማጠናከርና የኢኮኖሚ ትስስሩን ለማጎልበት እንደ አጋዥ ሃይል ናቸው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ብልጽግና ለማምራትና የተጀመረውን አዲስ ምዕራፍ ለማሳደግ በተለይም መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ በሁለቱም ሀገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም በዚህ ረገድ ምን መስራት እንዳለባቸው መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ የሚገናኙበትን መድረክም መፍጠር ይገባል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነት የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልጉት አልነበረም፡፡ ችግሩ በህጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይፈልግ ነበር፤ በተደጋጋሚ ጥያቄም ይቀርብ ነበር፡፡ ሆኖም በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ሳይፈታ ቀርቶ ወደ ጦርነት ሊያመራ ችሏል፡፡ የተደረገው ጦርነት በሀገራቱ ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ አልፏል፡፡ ግንኙነት ተቋርጦ የቆየባቸው 20 ዓመታት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝቦች አስቸጋሪ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ብዙ ዋጋ ካስከፈለው ‹‹ሞት አልባ ጦርነት›› ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸው የሚያስደስት ነው፡፡ ‹‹ያለፉት ዓመታት ለሁለቱም ህዝቦች የጨለማ ዘመን ነበሩ፡፡ ይህ የጨለማ ዘመን አልፎ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገራቸው በጣም ደስ ብሎኛል›› ያሉት አቶ ሰለሞን መላው የኤርትራ ህዝብም ችግሩ በመፈታቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው አብራርተዋል፡፡

የደርግን ሥርዓት ለመገርሰስ በተደረገው ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች መዘዋወራቸውንና በአዲስ አበባም ስድስት ወር እንደቆዩም ተናግረው፤ የኢትዮጵያን ህዝብ በመልካምነቱ እንደሚስታውሱት ጠቅሰዋል፡፡ የኤርትራ ህዝብም በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ፍቅር እንዳለው አንስተዋል፡፡

‹‹የደርግን ሥርዓት ለመገርሰስ በተደረገው ጥረት ሁለቱም ህዝቦች ያንን ሁሉ የሰው ህይወት የገበሩት፤ የኤርትራ ታጋዮች እስከ አዲስ አበባ ድረስ የታገሉት አዲስ የመተሳሰብ እና የመተጋገዝ ምዕራፍ እንዲከፍት ነበር›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡ ያለፉት 20 ዓመታት የሁለቱም ሀገራት የኪሳራ ዘመን ነበሩ›› ይላሉ፡፡

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅትም ህዝቡ በጠላትነት አይተያይም ነበር፡፡ አሁንም በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጥላቻ የለም፡፡ ይህንንም ህዝቡ በተግባር እያሳየ ሲሆን፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው መልካም ግንኙነትም ህዝቡ ስለሚፈልገው የመጣ ነው፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የሚፈልጉትን አግኝተዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ ሀገራቱ ላለፉት 20 ዓመታት ሰሞኑን ባለው አይነት አካሄድ ተጉዘው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ደረጃ ላይ ይደርሱ ነበር፡፡ አሁን የሁለቱንም ሀገራት ኪሳራ ለማካካስ የሚያስችል ጊዜ ተፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብም ካጋጠማቸው ኪሳራ ሊማሩበት ይገባል፡፡ ካለፈው ብዙ ትምህርት ቀስመዋል፡፡ ጦርነት ፋይዳ እንደሌለው እና ሰላም ለሁለቱም ህዝቦች መልካም ነገር እንደሆነ ተምረዋል፡፡
በእነዚያ 20 ዓመታት የሁለቱም ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ያቀርቧቸው የነበሩት አሉታዊ ዘገባዎችና ፕሮፖጋንዳዎች ለጦርነቱ እንጂ ለሰላም የሚበጁ ባለመሆናቸው፤ አሁን በቀድሞው መንገድ እንደማይቀጥሉ ሙሉ እምነታቸው መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የሓዳስ ኤርትራ ጋዜጣ የቦርድ አባል አቶ ዮሴፍ ኃይለማርያም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሁለቱ ሀገራት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው መስራት አለባቸው፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የነበረውን የጥል ግድግዳ የማፍረስ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን በጎ ስሜት ማሳየት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ የኤርትራ መገናኛ ብዙሃን ይህንኑ ማድረግ አለባቸው፡፡

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ለብዙ ሺ ዘመናት አብረው የነበሩ እንደመሆናቸው በርካታ የጋራ ነገሮች አሏቸው የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ነገሮች ኤርትራ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የሁለቱ ሀገራት መገናኛ ብዙሃንም እነዚህን የጋራ እሴቶች ለአድማጮቻቸው ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ሓዳስ ኤርትራ ጋዜጣም ይህን የሚያንጸባርቁ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ሀገራቱ አንድ የሚያደርጋቸው በርካታ ጉዳዮች ስለመኖራቸው፤ በአንድነት ማደግና መልማት እንዳለባቸው፤ የንግድ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማሳለጥ እንዳለባቸው በዜናዎቹ እና በሌሎች ዘገባዎቹ ይዳስሳል፡፡

የሓዳስ ኤርትራ ነባር ጋዜጠኛ አቶ ተስፋዓለም የማነም አስተያየት ከሰጡት የዝግጅት ክፍሉ ባልደረባ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው የሚናገሩት በትግርኛ ስለነበር በአስተርጓሚ ሃሳባቸውን ባካፈሉን ወቅት በቅድሚያ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ጉብኝት ያደረጉበት ቀን በህይወት ዘመኔ በጣም የተደሰትኩበት ነው›› በማለት ነበር የጀመሩት፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስለኤርትራ አሉታዊ ዘገባዎችን ይዘግቡ እንደነበር ሁሉ በኤርትራ በኩሉም ተመሳሳይ ነገር መኖሩን አስታውሰዋል፡፡ አንዱ ሀገር ስለሌላኛው የሚያሰራጨውን ዘገባ አጸፋ የመመለስ ስራ ሲከናወን እንደነበር ገልጸው፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስመራ ሲመጡ ህዝቡ ወጥቶ ያደረገላቸው አቀባበል ሲሰበክ ከነበረው ጥላቻ ይልቅ በህዝቡ ውስጥ ፍቅር እንደነበር አመላካች ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሁኔታው ህዝቡ ውስጥ ይህን ያህል ፍቅር ከነበረ ለምን 20 ዓመት ሙሉ እንዲሁ አለፈ የሚያስብል ነው›› የሚል ጥያቄ በውስጣቸው እንዳጫረባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሆኖም በስተመጨረሻ ፍቅር አሸንፏል፡፡ አሁን እየመጣ ያለው ፍቅር እና አንድነት ለዘላለም እንዲቀጥልም ምኞቴ ነው›› ብለዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ዳንኤል በቀለ –  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram