fbpx

ለ15 ደቂቃዎች የዘለቀው ጋብቻ

ከሰሞኑ ከወደ ዱባይ የሆነው ነገር በማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ በመሆን የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ማንነቱ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ለትዳር ካጫት ወጣት ጋር ጋብቻ የሚፈጽምበት ቀን ይደርስና ጋብቻው ወደሚከናወንበት ስፍራ ያመራል።

በዕለቱ ጋብቻውን በሼሪዓ ህግ መሰረት በሼሪዓ ጽህፈት ቤት በመገኘት የጋብቻ ፊርማ ይፈራረማል፤ ከዚያም ጋብቻው ወደ ሚጸድቅበት ፍርድ ቤት በማምራትም ጋብቻቸውን እውን ያደርጋሉ።

ታዲያ ግለሰቡ ይህን ጋብቻ ለመፈጸም አንድ ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ለሚስቱ አባት ወይም አማቹ በጋብቻ ስምምነቱ መሰረት በጥሎሽ መልክ ገንዘብ መክፈል ይኖርበታል።

ለዚህ ደግሞ አዲሱ ሙሽራ 100 ሺህ ድርሃም ለመክፈል ተስማምቷል፤ 50 ሺህ ድርሃሙን ሲፈራረሙ ቀሪውን 50 ሺህ ድርሃም ደግሞ ጋብቻቸውን አጽድቀው የሼሪዓ ፍርድ ቤቱን ሲለቁ ለመክፈል ተስማምቷል።

በዚህም የመጀመሪያውን 50 ሺህ ድርሃም ሲፈራረሙ ይከፍላል፤ ከዚያም ለጋብቻቸው እውቅና የሰጠውን የሼሪዓ ፍርድ ቤት ህንጻ ለቀው መውጣት ይጀምራሉ።

በዚህ መሃል የሚስት አባት ቀሪውን ገንዘብ እንዲያመጣ ይጠይቁታል፤ አዲሱ ሙሽራም “ህንጻውን ለቀን እንውጣና ቀሪውን 50 ሺህ ድርሃም ከተሽከርካሪየ አውጥቸ እሰጥሃለው” በማለት ይመልስላቸዋል።

ይህን መታገስ ያልፈለጉት የሙሽሪት አባት ግን “ቀሪውን ገንዘብ ሳትከፍል ህንጻውን መልቀቅ አትችልም፤ ዘመድህን አልያም ጓደኛህን ወደ ተሽከርካሪህ በመላክ ቀሪውን ገንዘብ አሁኑኑ አስረክበኝ” በማለት ይመልሱለታል።

እርሱ ግን ተሽከርካሪየ እስከምደርስ ይታገሱኝ በማለት ቢጠይቃቸውም የሙሽሪት አባት አይሆንም አሁኑኑ አምጣ በማለት ያስጨንቁታል።

ከ5 ደቂቃ ያነሰ ጊዜ መታገስ ያቃታቸው የሙሽሪት አባት ድርጊት ያበሳጨው ሙሽራም ያልተጠበቀውንና አነጋጋሪውን ውሳኔ አሳልፏል።

ከተጋቡ ደቂቃዎች እየቆጠሩ ባለበት ሰዓት በሁኔታው የተበሳጨው ሙሽራ ወደ ፍርድ ቤቱ ህንጻ ዳግም በመመለስ ጋብቻውን ቀዶታል።

ይህም ከተጋቡ ከ15 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ነው ተብሏል፤ ሙሽራው በወቅቱ በሙሽሪት አባት ድርጊት በመበሳጨት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

የወደፊት አማቹ ሊሆኑ የተዘጋጁት ግለሰብ ድርጊት የሰደቡኝ ያክል ተሰምቶኛልም ነው ያለው ሙሽራው።

ከዚህ ባለፈም አካሄዳቸው እጅጉን የተናኩ ያክል መጥፎ ስሜት ፈጥሮብኛል ሲልም ስለሁኔታው አስረድቷል።

ብዙ የታሰበው ጋብቻም በሙሽሪት አባት ትዕግስት ማጣት ከ15 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን አግኝቷል።

 

 

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራልና ገልፍ ኒውስ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram