fbpx

ለኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶች ጨረታ በአማካይ በካሬ ሜትር 30 ሺሕ ብር ቀረበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ የንግድ ቤቶችን ለመሸጥ ባወጣው ጨረታ በአማካኝ ለአንድ ካሬ ሜትር እስከ 30 ሺሕ ብር የመጫረቻ ዋጋ ቀረበ፡፡

 በ14ኛ ዙር የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶች ጨረታ አንድ ተወዳዳሪ በካሬ ሜትር 60 ሺሕ ብር ሲቀርብ፣ በአንፃራዊነት ቀደም ሲል ከተካሄዱ ጨረታዎች አነስተኛ ዋጋ የቀረበበትና በርካታ ተወዳዳሪዎችም የተሳተፉበት ነው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የቤት ርክክብና ማስተላለፍ ዋና የሥራ ሒደት መሪ ወ/ሮ አፀደ ዓባይ ለሪፖርተር  እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው ቀደም ሲል በተካሄዱ ጨረታዎች ከታዩ ችግሮች በመማር አዲስ የንግድ ቤቶች ሽያጭ መመርያ አውጥቷል፡፡

በዚህ መመርያ አንድ ተጫራች በአንድ ሳይት ከሦስት ንግድ ቤቶች በላይ መጫረት እንዳይችል በመደረጉ በርካታ ተሳታፊዎች እንዲወዳደሩ፣ ውድድሩም ፍትሐዊ እንዲሆን በመደረጉ ያልተጋነነ ዋጋ በካሬ ሜትር መቅረቡ ተመልክቷል፡፡

ቀደም ባሉት ጨረታዎች አቅም ያላቸው ነጋዴዎች፣ ባንኮችና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በርካታ ቤቶች ለመግዛት ከመጫረታቸውም በላይ የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ ፍትሐዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ከተውት ነበር ተብለው ይወቀሱ ነበር፡፡

በ13ኛው ጨረታ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት 45 ሱቆችን ለመግዛት ተወዳድሮ ከእነዚህ ውስጥ 33 አሸንፎ ውል ተዋውሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ውል ከተዋዋለ በኋላ 15 ሱቆችን እንደተወ ታውቋል፡፡

ወ/ሮ አፀደ እንደገለጹት ይኼን ዓይነት አሠራር በማስቀረት በተለይ መካከለኛ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎችን የሱቅ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኤጀንሲው ይኼንን ያልተገባ አሠራር አስተካክሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ከ175 ሺሕ በላይ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡ ባለፉት 13 ዙሮች ከ12,500 በላይ ንግድ ቤቶች በጨረታ አስተላልፏል፡፡

በ14ኛው ዙር ጨረታ 2,331 የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶች ለማስተላለፍ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጨረታ የወጣ ሲሆን፣ 33 ሺሕ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት የጨረታ ሰነድ ገዝተው እየተወዳደሩ ነው፡፡

ጨረታው የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከፈተ ሲሆን፣ ከተወዳዳሪዎች ብዛት አንፃር እስካሁን የጨረታ ሳጥን እየተከፈተ አሸናፊዎች እየተለዩ ነው፡፡ ወ/ሮ አፀደ እንደሚሉት፣ እስካሁን እየቀረበ ያለው ዋጋ ካለፉት ጨረታዎች ጋር ሲነፃፀር የተረጋጋ ነው፡፡

በ13ኛው ጨረታ 2,160 ንግድ ቤቶች ለጨረታ ሲቀርቡ፣ እነዚህን ቤቶች ለመግዛት 20 ሺሕ ነጋዴዎች የጨረታ ሰነድ ወስደዋል፡፡ በጨረታው በአማካይ በካሬ ሜትር 45 ሺሕ ብር ሲቀርብ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው ግን 101 ሺሕ ብር በካሬ ሜትር ነው፡፡

ሪፖርተር
Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram