fbpx
AMHARIC

ለንግድ የማይውሉ ወደ ሀገር የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ተሻሽሎ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ለንግድ የማይውሉ ወደ ሀገር የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎችን በሚመለከት የወጣው መመሪያ ተሻሽሎ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ።

በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የወጣው የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ መተግበር ከጀመረ ሶስተኛ ወሩን ይዟል።

መመሪያው ዓለም አቀፍ መንገደኞች ወደ ሀገር ሲገቡ እና ከአገር ሲወጡ የግል መገልገያዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እና ቀረጥ ከፍለው እንዴት መስተናገድ አለባቸው የሚለውን የያዘ ነው።

በኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የአምራች እና የወጪ ንግድ ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ በየነ፥ መመሪያውን የበርካታ ዓመታት የዜጎችን ጥያቄ የመለሰ ይሉታል።

የዜጎችን ጥያቄ ይመልሳል የተባለው መመሪያ ግን መተግበር ከጀመረ በሶስት ወር ውስጥ እንዲሻሻል ከውሳኔ ላይ ተደርሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል።

ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ፥ መመሪያው እንዲሻሻል ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ምክንያት መሬት ላይ ሲተገበር የታዩ ክፍተቶች መታየታቸው ነው ይላሉ።

መመሪያውን ለማሻሻል ምክንያት ከሆኑ አንቀፆችን ውስጥ የተወሰኑትን በማሳያነት በማቅረብ፤ በግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ቁጥር 52/2010 ውስጥ ግልፅ ያልሆኑ አንቀፆች ተስተውለዋል ነው የሚሉት።

አቶ ሙልጌታ፥ “በመመሪያው ላይ ለተገልጋዮች በሚገባ ቋንቋ ያልተፃፉ እና ግልፅ ያልሆኑ ድንጋጌዎች መኖራቸውን በሂደት ተገንዝበናል” ያሉ ሲሆን፥ ለምሳሌ “ከመንገደኛ ተለይቶ የሚመጣ ሻንጣ” የሚለው ግልፅ አልበረም ብለዋል።

ሌላው የመንገደኛ ትርጉምን በተመለከተ፤ የበረራ ሰራተኞችንና የአጓጓዥ ድርጅት ሰራተኞችን ያካትታል አያካትትም የሚለው፤ ምንም እንኳ ቃሉ መንገደኛ በሚል ቢታወቅም በግልፅ ቋንቋ አለመፃፉ በክፍተትነት መታየቱን አንስተዋል።

አቶ ሙሉጌታ በየነ፥ መመሪያው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ተከትሎ ከታሰበለት አላማ ውጭ እንደይሆን የሚሉ ድምፆች ከየአቅጣጫው መሰንዘራቸውን ይናገራሉ።

ዳይሬክተሩ ይህንን ሁኔታ ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ህግ ወጦች ተደርሶባቸዋል ያሉት አቶ በየነ፥ እነዚህ ህገ ወጦች የፈፀሟቸውን ተግባራት እና በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄዳባቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

መመሪያው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የተፈቀደ ነው የሚለው ላይም፥ አቶ ሙሉጌታ ይሄን ጥያቄ ለባለስልጣኑም እየደረሰ ያለ መሆኑን ተናግረው፤ መመሪያው ግን ከሚነሳው ጥያቄ በተቃራኒው ዘላቂ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።

ተሻሽሉ የሚወጣው የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ለተጠቃሚዎች ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram